የሰላም ስምምነቱ ሀገሪቱ የጀመረችውን የልማትና የእድገት ጉዞን ወደ ፊት ለማራመድ የጎላ ሚና አለው - የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች - ኢዜአ አማርኛ
የሰላም ስምምነቱ ሀገሪቱ የጀመረችውን የልማትና የእድገት ጉዞን ወደ ፊት ለማራመድ የጎላ ሚና አለው - የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች
አዳማ፤ ህዳር 27/2017(ኢዜአ)፡- የሰላም ስምምነቱ ሀገሪቱቷ የጀመረችውን የልማትና የእድገት ጉዞ ወደ ፊት ለማራመድ የጎላ ሚና ያለው መሆኑን የአዳማ ከተማ የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች ገለጹ።
ታጣቂዎቹ የህዝቡን ችግርና የሀገር ሽማግሌዎችን ተማፅኖ በመገንዘብ ወደ ሰላም ስምምነቱ በመምጣታቸው ምስጋናና ክብር ይገባቸዋል ሲሉም ተናግረዋል አስተያየት ሰጪዎቹ።
ከሽማግሌዎቹ መካከል አቶ ፋይሳ መገርሳ እንደገለጹት ከጦርነት የሚገኝ ትርፍ የለምና የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት የህዝቡን ችግር በመገንዘብ የሰላም አማራጭ ወስደው ከስምምነት በመድረሳቸው እጅግ ምስጋና ይገባቸዋል።
በአሁኑ ወቅት በክልሉ አዝመራ የሚሰበሰብበትና የነገው ሀገር ተረካቢ ተማሪዎች የሚማሩበት ጊዜ ነው ያሉት አቶ ፈይሳ፤ ይህም ለአርሶ አደሮች፣ ለተማሪዎች፣ ለኦሮሞ ህዝብና ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ እፎይታ የሰጠ ስምምነት ነው ብለዋል።
ባለፉት ዓመታት በክልሉ በነበረው ችግር ገበሬው እንዳያርስ፣ ተማሪው እንዳይማር፣ ሠራተኞች በአግባቡ ስራቸውን እንዳይሰሩ፣ ልማትና እድገት ወደ ኋላ እንዲመለስና በድህንትና ኋላቀርነት ውስጥ እንድንቆይ ያደረጉን ጥረቶችን ያከሸፈ የሰላም ስምምነት መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።
ህዝቡ ከጦርነት የሚገኝ ትርፍ የለም በማለት ለጥይትና መሳሪያ ግዥ የሚወጣው የሀገር ሀብት ለትምህርት ቤቶች፣ ለሆስፒታሎችና ለሌሎች መሰረተ ልማት ግንባታ በማዋል ሀገራችን ከድህንነት እንድትወጣ ማድረግ አለብን ነው ያሉት።
እርቀ ሰላም በመውረዱ ደስተኞች ነን ያሉት ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ሃጂ ሁሴን ሀሞ፤ ይሄ እርቅ እንዲመጣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ አባ ገዳዎች፣ ሃዳ ሲንቄዎችና ህዝቡ ከመንግሥት ጎን ሆነው ያደረጉት ጥረት ፍሬ ማፍራቱን ማሳያ ነው ብለዋል።
በዚህም ለኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት አመራሮችና ለመንግስት ትልቅ ክብርና ምስጋና ይገባቸዋል ያሉት ሃጂ ሁሴን፤ የተቀሩትም ይሄን ፈለግ በመከተል የሰላም አማራጭ ወስደው መግባት አለባቸው ብለዋል።
በዚህ ያለፈውን ጊዜ በመካስ ሀገራችን በእንድነት ወደ ፊት ማራማድ አለብን ብለዋል።
የሰላምና የእርቅ ጉዞ ጅማሬው የዜጎችን ሰርቶ የመለወጥ፣ ከወዳጅ ዘመድ ጋር ለመገናኘት ችግር የሆኑትን ማነቆዎች የሰበረ ነው ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ የሃይማኖት አባት አባ አዲስ ነጋሽ ናቸው።
የተገኘው እርቀ ሰላም ለኦሮሞ ህዝብና ኦሮሚያ ብቻ ሳይሆን ለመላው ኢትዮጵያ ሰላም እንዲመጣ በር የከፈተ መሆኑን ጠቅሰው ስምምነቱ ለመላው ኢትዮጵያ ቱሩፋት ስለሆነ ሌሎችም ይሄንን ምሳሌ መከተል አለባቸው ብለዋል።