ቀጥታ፡

የጋምቤላ ክልልን የቱሪዝም ሃብቶች በአግባቡ በማልማት ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ማሳደግ ይገባል- የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 27/2017(ኢዜአ)፦ የጋምቤላ ክልልን የቱሪዝም ሃብቶች በአግባቡ በማልማት ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ማሳደግ እንደሚገባ የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ ገለጹ።

ሚኒስትሯ ከክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ አለሚቱ ኡሞድ ከፌዴራልና ከክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ጋር ተወያይተዋል።

በውይይቱም ሚኒስትሯ የጋምቤላ ክልል ለቱሪዝም ኢንዱስትሪው እድገት አጋዥ የሆኑ የተፈጥሮ ሃብቶች ያሉበት አካባቢ መሆኑን ገልጸዋል።


 

የቱሪዝም ሀብቱ ለብዝሃ ኢኮኖሚ ከሚኖረው ፋይዳ ባለፈ ለዜጎች የስራ ዕድል በመፍጠር ረገድ የላቀ ሚና አለው ብለዋል።

በመሆኑም ይህንን የተፈጥሮ ሃብት በአግባቡ አልምቶ ከመጠቀም አንፃር ያሉ ውስንነቶችን በጋራ በመፍታት የዘርፉን ጥቅም ማስጠበቅ ይገባል ነው ያሉት።

በተለይም የጋምቤላ ብሔራዊ ፓርክ በሃገሪቱ ካሉ ፓርኮች መካከል በስፋቱና በዱር እንስሳት ሀብቱ እጅግ ግዙፉ መሆኑን ተናግረዋል።

በመሆኑም አሁን ላይ ብሔራዊ ፓርኩን ከአፍሪካ ፓርክ ጋር በማስተሳሰር ለማልማት ግብ ተጥሎ ተግባራዊ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው ለስኬታማነቱ በጋራ ልንሰራ ይገባል ብለዋል ሚኒስትሯ።


 

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ አለሚቱ ኡሞድ በበኩላቸው በክልሉ የጋምቤላ ብሔራዊ ፓርክን ጨምሮ ሰፊ የቱሪዝም ሃብት መኖሩን ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ ካሁን በፊት ለዘርፉ የተሰጠው ትኩረት ዝቅተኛ በመሆኑ ሀብቱ በሚፈለገው ልክ ለምቶ ለክልሉ ብሎም ለሀገሪቱ ማበርከት ያለበትን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም አለማስገኘቱን ተናግረዋል።

በመሆኑም አሁን ላይ ለዘርፉ በተሰጠው ልዩ ትኩረት ሀብቱን በሚፈለገው ደረጃ በማልማት ጥቅም ላይ ለማዋል ሰፊ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝም ገልፀዋል።

የጋምቤላ ብሔራዊ ፓርክ ከአፍሪካ ፓርኮች ጋር በማስተሳሰር ለማልማት የተጀመረው ጥረት ለዘርፉ የተሰጠውን ትኩረት የሚያመላክት መሆኑን በማሳያነት ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን መኮነን በዚሁ ጊዜ እንዳሉት የጋምቤላ ብሔራዊ ፓርክ በብዝሃ ህይወት ሀብቱ በሀገሪቱ ከሚገኙ ብሔራዊ ፓርኮች በቀዳሚነት የሚጠቀስ ነው።

በተለይም ፓርኩን በመሠረተ ልማት በማስተሳሰር ወደ ሀብት ለመቀየር ሲባል ከአፍሪካ ፓርኮች ጋር በመተባበር ለማልማት እየተሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

ይህም የቱሪዝም ዘርፉን በማነቃቃትና ለሀገሪቱ የሚያስገኘውን ጥቅም ለማስጠበቅ ትልቅ አቅም የሚፈጥር መሆኑን አብራርተዋል።

ትላንት ምሽት በተካሔደው ውይይት ላይ የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ እና የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ አለሚቱ ኡሞድን ጨምሮ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም