ቀጥታ፡

ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥና ሙስናን የሚፀየፍ ትውልድ ለመፍጠር እየተሠራ ነው-ኮሚሽነር ጀማል ረዲ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 27/2017(ኢዜአ)፡- በአዲስ አበባ ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥና ሙስናን የሚፀየፍ ትውልድ ለመፍጠር እየተሠራ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስነ ምግባር እና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀማል ረዲ ገለጹ።

የአዲስ አበባ የስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር "ስነ ምግባራዊ ትውልድ ለሁለንተናዊ ብልጽግና" በሚል መሪ ሀሳብ ያዘጋጁት የፓናል ውይይት በዓድዋ ድል መታሰቢያ እየተካሄደ ነው።


 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስነ ምግባር እና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀማል ረዲ፥ በመክፈቻ ንግግራቸው፥ ሙስና ሀገር እና ህዝብን አደጋ ላይ የሚጥል እኩይ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።

ኮሚሽኑ የሙስናን አስከፊነት ህብረተሰቡ በመገንዘብ የሙስና መከላከል ሥራዎችን እንዲያግዝ የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫዎችን እየፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይም ወጣቱ ትውልድ ሙስናን የሚጸየፍና በስነ ምግባር የታነጸ እንዲሆን የሞራል ግንባታ ስራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል።

ሙስናን መከላከል የሚያስችሉ የተለያዩ የንቅናቄ መድረኮች እየተካሄዱ ነው ያሉት ኮሚሽነሩ፥ የዛሬው የፓናል ውይይትም የዚሁ አካል መሆኑን ተናግረዋል።

በቀጣይም ሙስናን ለመከላከል የሚያስችሉ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቁመዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የሰላም፣ ፍትህና መልካም አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ሙሉነህ ደሳለኝ በበኩላቸው፥ ሌብነት እና ብልሹ አሰራር የሀገር እድገት ጸር መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ትልቅ ደረጃ እንዳትደርስ ካደረጓት ችግሮች አንዱ ሙስና ነው ያሉት የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢው፥ በአዲስ አበባ ሙስናን የመከላከል ሥራዎች ውጤት እያመጡ መሆናቸውን አስረድተዋል።

ከሃይማኖት ተቋማትና ከትምህርት ቤቶች ጋር በመተባበር በወጣቱ ትውልድ የስነ ምግባር ግንባታ ላይ በርካታ ስራዎች መከናወናቸውን ጠቅሰው፥ የፓናል ውይይቱም አጋዥ ነው ብለዋል።


 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ ሰይፈ ደርቤ፥ ኢዜአ ለሀገር ገፅታ እና ለትውልድ የስነምግባር ግንባታ እንዲሁም ለብሔራዊ መግባባት በትኩረት እየሠራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ኢዜአ የአዲስ አበባ የለውጥ ማዕከልነትን የሚያጎሉ ስራዎችን ለዓለም እያስተዋወቀ እንደሚገኝ የገለጹት ዋና ስራ አስፈጻሚው፥ በቀጣይ ተልዕኮውን ለማሳካት በትጋት ይሰራል ብለዋል።

ሀገራዊ ትልሞችን ለማሳካት እንዲሁም ሙስናና ብልሹ አሰራርን ለመከላከል አጋዥ የሆኑ የፓናል ውይይቶችን በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች እያካሄደ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በመድረኩ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ ረዳት ፕሮፌሰር ምህረቱ ሻንቆ(ዶ/ር)፣ በአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የሰላም፣ ፍትህና መልካም አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ሙሉነህ ደሳለኝ፣የአዲስ አበባ የስነ ምግባር እና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀማል ረዲ፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው፣ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ ሰይፈ ደርቤ እና ሌሎች የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

መድረኩ ከሙስና የጸዳ ከተማ እና ሀገር ለመፍጠር በሚደረገው ሂደት ውስጥ ህብረተሰቡ አጋዥ እንዲሆን የጋራ አረዳድ ለመፍጠር ያለመ መሆኑ ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም