ቀጥታ፡

በአገር አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ በሚደረገው ሁለተኛው ዙር የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ ወደ 6 ሚሊዮን የሚጠጉ ህጻናት ይከተባሉ

ህዳር 27 /2017 (ኢዜአ) ፡-በአገር አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ በሚደረገው ሁለተኛው ዙር የልጅነት ልምሻ (ፖሊዮ) ክትባት ወደ 6 ሚሊዮን የሚጠጉ ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ህጻናት እንደሚከተቡ የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

ሀገር አቀፉ የፖሊዮ ክትባት ማስጀመሪያ መርሃ ግብር የፌዴራልና የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት ዛሬ በጋምቤላ ከተማ በይፋ ተካሄዷል። 


 

በኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የፖሊዮ ወረርሽኝ ምላሽ አስተባባሪ አቶ ሚኪያስ አላዩ እንደገለፁት ከዛሬ ጀምሮ ጋምቤላ ክልልን ጨምሮ በሃገሪቱ በሚገኙ የተለያዩ ክልሎች ዕድሜያቸው ከ5 ዓመት በታች ለሆኑ ህፃናት በዘመቻ ቤት ለቤት የፖሊዮ ክትባት መስጠት ተጀምሯል። 

ከዛሬ ህዳር 27/2017 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ አራት ቀናት በሚሰጠው በዚሁ የክትባት ዘመቻ  ከ5 ነጥብ 8 ሚሊዮን የሚበልጡ ህፃናት እንደሚከተቡ ገልፀዋል። 

ክትባቱ ከሚሰጥባቸው ክልሎች መካከል ጋምቤላ፣ አማራ፣ አፋር ፣ሶማሌ፣ ኦሮሚያ እና ሌሎችም እንደሚገኙበት አቶ ሚኪያስ ገልፀዋል። 

የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አቤል አሰፋ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ዛሬ በተጀመረው የክትባት ዘመቻ በክልሉ በሚገኙ ሁሉም ወረዳዎችና የስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች ከ159 ሺህ በላይ ህፃናት ይከተባሉ። 


 

ሀገር አቀፉ የክትባት ማስጀመሪያ መርሃ ግብር በጋምቤላ ክልል ሊካሄድ የቻለው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የበሽታው ምልክት እየታየ በመምጣቱ መሆኑንም ተናግረዋል ። 

በክልሉ ከፖሊዮ ክትባት ማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ በተጨማሪ አለም አቀፉ የፖሊዩ ቀን በፓናል ውይይት እንደሚከበርም ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም