የተተኪ እና ነባር አመራሮች የልምድ ልውውጥ መድረክ በኢትዮጵያ የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን ለማሳካት የላቀ ሚና አለው - አቶ ዛዲግ አብርሃ - ኢዜአ አማርኛ
የተተኪ እና ነባር አመራሮች የልምድ ልውውጥ መድረክ በኢትዮጵያ የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን ለማሳካት የላቀ ሚና አለው - አቶ ዛዲግ አብርሃ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 27/2017(ኢዜአ)፡- የተተኪ እና ነባር አመራሮች የልምድ ልውውጥ መድረክ በኢትዮጵያ ተጀምረው ያልተቋጩ ፕሮጀክቶችን ለማሳካት የላቀ ሚና አለው ሲሉ የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ፕሬዝዳንት አቶ ዛዲግ አብርሃ ተናገሩ።
አካዳሚው የአመራር ልምድ ልውውጥ ሥራዎች ስኬታማ እንዲሆኑ ሚናውን መወጣቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ኢኒስፓየርድ ዲቭሎፕመንት ከተሰኘው ድርጅት ጋር በመተባበር ያዘጋጀው "ነጸብራቅ የመሪነት ጉባኤ" በመካሄድ ላይ ይገኛል።
ጉባኤው በተተኪ አመራሮችና በነባር አመራሮች መካከል ልምድ ልውውጥ ማድረግን ያለመ ሲሆን ከሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች የተውጣጡ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት አመራሮች፣ የእምነት አባቶች፣ የቢዝነስ መሪዎች የሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎችና የመንግሥት አመራሮች በጋራ የሚመክሩበት መድረክ ነው።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በይፋ ያስጀመሩት መርሃ ግብር ለሚቀጥሉት ሦስት ቀናት የሚካሄድ ሲሆን ከ600 በላይ ሰዎች ተሳትፈውበታል።
የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ፕሬዝዳንት አቶ ዛዲግ አብርሃ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት፤ ሀገርን የሚያሻግሩ ፕሮጀክቶችን እውን ለማድረግ በተተኪ እና ነባር አመራሮች መካከል የሚኖረውን ቅብብሎሽ ማሳለጥ ይገባል።
በአመራሩ መካከል የሚፈጠረው ሕብረት ለሀገራዊ ፕሮጀክቶች ቀጣይነት መረጋገጥ ትልቅ ሚና እንዳለውም ጠቁመዋል።
ሀገርን ለማሻገርና ሁለንተናዊ ለውጥ ለማምጣት የትውልዶች ቅብብሎሽና ህልም መጋራት አለባቸው ያሉት ፕሬዝዳንቱ መሰል የአመራሮች ልምድ ልውውጥ መድረክ ትልቅ ፋይዳ አለው ብለዋል።
የንግድ ተቋማት፣ ትምህርት ቤቶች፣ የሲቪል ማህበረሰብ እንዲሁም የመንግሥት አመራሮች በጋራ የሚሰሩበት አውድ መፍጠር ወሳኝ መሆኑንም አንስተዋል።
በተተኪና ነባር አመራሮች መካከል የተጀመረው የልምድ ልውውጥ መልካም መሆኑን የጠቀሱት አቶ ዛዲግ ይህ ልምድ መስፋትና ተደራሽ መሆን እንደሚኖርበት አመልክተዋል።
የአመራር ልምድ ልውውጡ ስኬታማ እንዲሆን አካዳሚው ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በመተባበር የሚጫወተውን ሚና እንደሚያጠናክርም ተናግረዋል።
የኢኒስፓየርድ ዲቭሎፕመንት ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ወጣት ልዩነህ ታምራት፤ መርሃ ግብሩ በሥነ ምግባራቸው፣ በአመራር ክህሎታቸውና ልምዳቸው ምሳሌ የሆኑ አመራሮች ልምዳቸውን የሚያጋሩበት መድረክ መሆኑን ገልጿል።
ለዚህም ከፍተኛ አመራሮች ጭምር ተጋብዘው ክህሎታቸውን የሚያካፍሉ ሲሆን ስልጠናዎች፣ የፓናል ውይይቶች እና የእርስ በእርስ ግንኙነቶች የሚጠናከሩበት መድረኮች ናቸው ሲልም ተናግሯል።
ተተኪው አመራር በቂ እውቀት የጨበጠ፣ በቂ ልምድና አቅም ያካበተ እንዲሆን የሚደረጉ ጥረቶች እንዲሳኩ ድርጅቱ ሀገራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት ግብ ይዞ ወደ ሥራ መግባቱንም ገልጿል።
በዚህ ረገድ ድርጅቱ የሚጠበቅበትን ሚና ለመወጣት ዝግጁ መሆኑንም አረጋግጧል።