ቀጥታ፡

የወደፊቱን የትራንስፖርት እና ኢነርጂ ዘርፍ ስትራቴጂ በመቅረፅ ሁሉንም የአፍሪካ ሀገራት ተጠቃሚ የማድረግ የጋራ ሃላፊነት አለብን - ዓለሙ ስሜ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ህዳር 27/2017(ኢዜአ)፡- የወደፊቱን የትራንስፖርት እና ኢነርጂ ዘርፍ ስትራቴጂ በመቅረፅ ሁሉንም የአፍሪካ ሀገራት ተጠቃሚ የማድረግ የጋራ ሃላፊነት አለብን ሲሉ የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ(ዶ/ር) ገለጹ።

የአፍሪካ ህብረት የትራንስፖርት እና ኢነርጂ ቴክኒካል ኮሚቴ ሶስተኛው ልዩ የሚኒስትሮች ስብሰባውን ትናንት በበይነ መረብ አካሂዷል።


 

በውይይቱ ላይ የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ሚኒስትሮች እና የዘርፉ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።

የአንድነት መርህን በመከተልና ወንድማማችነትን በማጠናከር የበለፀገች አፍሪካን እውን ማድረግ እንደሚገባ የትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ(ዶ/ር) ገልጸዋል።

ስብሰባው በአፍሪካ ትራንስፖርት እና ኢነርጂ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ መሆኑ ተገልጿል።

ውይይቱን በሰብሳቢነት የመሩት የትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ(ዶ/ር) የወደፊቱን የትራንስፖርት እና ኢነርጂ ዘርፍ ስትራቴጂ በመቅረፅ ሁሉንም የአፍሪካ ሀገራት ተጠቃሚ የማድረግ የጋራ ኃላፊነት አለብን ብለዋል።

የትራንስፖርት እና የኃይል ዘርፍ ለኢኮኖሚ እድገት፣ ለንግድ መሳለጥ እና ለኢንዱስትሪዎች እድገት ወሳኝ መሆናቸውን አመልክተዋል።

ቅንጅትና ትብብርን በማጎልበት፣ የአንድነት መርህን በመከተልና ወንድማማችነትን በማጠናከር የበለፀገች አፍሪካን እውን ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል።

የቴክኒክ ኮሚቴው በስብሰባው በትራንስፖርት የዘላቂ አቪዬሽን ኃይል ምንጭ ስትራቴጂ፣ የአቡጃ የሴፍቲ እና ኤር ናቪጌሽን ግቦችን እንደገና በመከለስ አፅድቋል።

ኢነርጂን በሚመለከት የአፍሪካ የኢነርጂ ውጤታማነት ስትራቴጂ እና አህጉራዊ የአረንጓዴ ሃይድሮጂን ስትራቴጂን ማፅደቁን ከትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም