ቀጥታ፡

ኮሚሽኑ ሙስናን በመከላከል ረገድ የቅንጅት አሰራርን ሊያጠናክር የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ከፌዴራል ፖሊስ ጋር ተፈራረመ

አዲስ አበባ፤ህዳር 27/2017(ኢዜአ)፦የፌዴራል የሥነ-ምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ሙስናን በመከላከል እና ህግን በማስከበር ዙሪያ የትስስር እና የቅንጅት አሰራርን ሊያጠናክር የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ከኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ጋር ተፈራረመ።

የፌዴራል የሥነ-ምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ሳሙኤል ኡርቃቶ (ዶ/ር)በወቅቱ እንዳሉት፥ ኮሚሽኑ ትውልዱን በሥነምግባር በማነፅና ሙስናን በመከላከል ረገድ በርካታ ስራዎችን እየሰራ ይገኛል፡፡


 

በቀጣይም ከኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ጋር በመቀናጀት  መረጃን መሰረት በማድረግ ሙሰኞችን ተጠያቂ የማድረግ ስራ በቅንጅት እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡

ሁለቱ ተቋማት በሥነምግባር ግንባታ እና ሙስና መከላከል ላይ ትስስራቸውን እንደሚያጠናክሩ ጠቁመዋል፡፡

ኮሚሽነሩ አክለውም፥ የመግባቢያ ስምምነቱ የሙስና ወንጀል መከላከልና የምርመራ ሥራን ዕውቀትና ብቃትን መሠረት ባደረገ መልኩ ለመስራት ትልቅ ዕድል ይፈጥራል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል በበኩላቸው፥ ከሀገራዊ ሪፎርሙ በኃላ የመንግስት ተቋማት በጋራ ተቀራርበው እና ተቀናጅተው የመስራት ባህል በከፍተኛ ደረጃ እያደገ ነው፡፡

የሙስና ወንጀልን ለመከላከል በሁለቱ ተቋማት የበለፀገውን ቴክኖሎጂ በጋራ አስተሳስሮ በመጠቀም የሚቀርቡ የሙስና መዝገቦች ላይ ጠንካራ ምርመራ በማድረግ ጠርተው ለአቃቢ ሕግ እንዲቀርቡ ስምምነቱ ትልቅ እድል ይፈጥራልም ብለዋል፡፡

ኮሚሽነር ጀነራሉ አያይዘውም፥ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የሙስና ወንጀልን በመከላከልና ሙስናን የሚፀየፍ ማህበረስብ እንዲፈጠር በሀገራችን እየተደረገ ያለውን ርብርብ በማገዝ ከፍተኛ ሥራ እያከናወነ መሆኑን አንስተዋል፡፡

በቀጣይም የሥነ-ምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ባለሙያዎችን በኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ በማሰልጠንና የተለያዩ ምርምርና ጥናቶችን በማካሄድ ድጋፍ እንደሚያደርግ መግለጻቸውን ከፌደራል የሥነ-ምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም