ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የአለም ንግድ ድርጅት አባል መሆን ለተቀረው አለም ተጨማሪ የገበያ ዕድሎችን የሚፈጥር ነው - ሻንግቼን ዣንግ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 26/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የአለም ንግድ ድርጅት አባል መሆን ለተቀረው አለም ተጨማሪ የገበያ ዕድሎችን የሚፈጥር ነው ሲሉ የአለም የንግድ ድርጅት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሻንግቼን ዣንግ ገለጹ።

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትሩ ካሣሁን ጎፌ(ዶ/ር) ከአለም ንግድ ድርጅት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ጋር ዛሬ በስዊትዘርላድ ጄኔቭ ከተማ ተወያይተዋል።

ውይይታቸውም ኢትዮጵያ በቅርቡ የምታካሂደውን 5ኛውን የዓለም ንግድ ድርጅት የስራ ላይ ቡድን የአባልነት ድርድር ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነው።

በዚህ ወቅት፥ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ እንዳሉት ኢትዮጵያ በፍጥነት እያደገ የመጣ ኢኮኖሚ ባለቤት ናት።

በመሆኑም የኢትዮጵያ የአለም ንግድ ድርጅት አባል መሆን ለተቀረው አለም ተጨማሪ የገበያ ዕድሎችን የሚፈጥር መሆኑን ገልጸው፥ በዚህ ረገድ የሚጠበቅባቸውን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ማረጋገጣቸውን ከንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም