"ሄር ኢሴ” ዓለም አቀፍ ቅርስ ሆኖ መመዝገብ የሶማሌ ኢሳ ማህበረሰብ አባላት በጋራ ጉዳዮቻቸው ላይ ያላቸውን ትብብር ይበልጥ የሚያጠናክር ነው - ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ኢብራሂም ኡስማን

አዲስ አበባ፤ ህዳር 26/2017(ኢዜአ) "ሄር ኢሴ ያልተጻፈ ባህላዊ ህግ ዓለም አቀፍ ቅርስ ሆኖ መመዝገቡ የሶማሌ ኢሳ ማህበረሰብ አባላት በጋራ ጉዳዮቻቸው ላይ ያላቸውን ትብብር ይበልጥ የሚያጠናክር መሆኑን የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ኢብራሂም ኡስማን ገለጹ።

የቅርሱ መመዝገብ የተሻለ ጥበቃና እንክብካቤ ለማድረግ እንደሚያግዝም አመልክተዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስ እና ባህል ድርጅት(ዩኔስኮ) የማይዳሰሱ የባህል ቅርሶች ጥበቃ የበይነ መንግስታት ኮሚቴ 19 መደበኛ ስብሰባውን ከሕዳር 23 ቀን 2017 . አንስቶ በፓራጓይ አሱንሲዮን እያደረገ ይገኛል።

ኮሚቴው ዛሬ እያደረገ ባለው ስብሰባ ላይ ኢትዮጵያ፣ ጅቡቲ እና ሶማሊያ በጋራ ያቀረቡት "ሄር ኢሴ" የሶማሌ ኢሣ ማኅበረሰብ ያልተጻፈ ባሕላዊ ሕግ በመልቲናሽናል ሰነድነት በሰው ልጆች ወካይ ዓለም አቀፍ የማይዳሰስ ቅርስነት መዝግቧል።


 

ቅርሱን የተመለከተ 22 ገጽ ሪፖርት ለስብሰባው ተሳታፊዎች ቀርቧል።

ሄር ኢሴ ባህላዊ መተዳደሪያ ህግ በሶማሌ ክልል ሲቲ ዞን 16ተኛው ክፍል ዘመን 44 የኢሣ ማህበረሰብ አባላት ተቀምጠው ያጸደቁት ነው።

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የሶማሌ ህዝብ አንድ አካል የሆነው ኢሳ ማህበረሰብ ህጉን ከትውልድ ወደ ትውልድ በቃል እየተቀባበለ እየተመራበትና በትውልድ ቅብብሎሽ እየዳበረ መጥቷል።

የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ኢብራሂም ኡስማን "ሄር ኢሴ" የሶማሌ ኢሣ ማኅበረሰብ ያልተጻፈ ባሕላዊ ሕግ በመልቲናሽናል ሰነድነት በሰው ልጆች ወካይ ዓለም አቀፍ የማይዳሰስ ቅርስነት በተመዘገበበት ስነ ስርዓት ላይ ተገኝተዋል።

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው የስልክ ቆይታ እንደገለጹት ሄር ኢሴ ባህላዊ ህግ በኢትዮጵያ፣ ጅቡቲ እና ሶማሊያ ያሉ የሶማሌ ኢሳ ማህበረሰብ አባላት በግልጽ አሰራር የሚፈጸም፣ በፍትሐዊነት እና በእኩልነት ማህበረሰቡን የሚያገለግል የፍትህ ስርዓት ነው።

ከዚህ አንጻር የሕጉ በቅርስነት መመዝገብ ለማህበረሰቡ የሚሰጠው ጠቀሜታ ከፍተኛ መሆኑን አመልክተዋል።

ህጉ በዋናነት ችግሮች ስር ሳይሰዱ እልባት በመስጠት የሚዳኝበት እና አሸናፊና ተሸናፊ ሳይኖር መፍትሔ በማበጀት ሰላምን ለማስፋን ያለው ፋይዳ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

ባህላዊ ህጉ ሃይማኖት እና መደበኛ ህግን የማይጸረርና ማህበረሰቡ 16ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ተስማምቶ አደረጃጀቶችና አሰራሮች የጸደቀ መሆኑን አመልክተዋል።

የረጅም ጊዜ የታሪክ እና የማንንት መገለጫ የሆነው ይሄ ህግ በየዘመኑ ትውልዱ የራሱን አሻራ ያሳረፈበት ማህበራዊ እሴት እንደሆነም ነው ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ያነሱት።

ባህላዊ ሕጉ መመዝገቡ ለህጉ ቀጣይነት ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያደርግና የሶስቱን አገራት ማህበረሰቦች በማስተባበር ሰላማቸው ዘለቄታዊ በሆነ መንገድ እንዲጠበቅ ከማድረግ አኳያ ቁልፍ ሚና አለው ብለዋል።

የማህበረሰብ አባላቱ ጉዳዮቻቸው ላይ በጋራ እንዲሰሩ ያለው አበርክቶ ጉልህ መሆኑን አንስተዋል።

በሦስቱም አገራት የሚኖሩ የማኀበረሰቡ አባላት የአስተዳደር ማዕከሉን በኢትዮጵያ ድሬዳዋ ከተማ ባደረገ አንድ መሪ ወይንም ኡጋስ እንደሚመሩ አመልክተዋል።

የህጉ መጽደቅ ቀጣናዊ ትብብርን ለማጎልበት እና የተቀናጀ የቅርስ እንክብካቤና ጥበቃ ስራ እንዲኖር አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም