የጋሞ አደባባይ ለአርባ ምንጭ ተጨማሪ የውበት አክሊል ሆኗል - ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ - ኢዜአ አማርኛ
የጋሞ አደባባይ ለአርባ ምንጭ ተጨማሪ የውበት አክሊል ሆኗል - ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ
አዲስ አበባ፤ ህዳር 26/2017(ኢዜአ)፡- የጋሞ አደባባይ ለአርባ ምንጭ ተጨማሪ ምልክትና የውበት አክሊል ሆኗል ሲሉ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ገለጹ።
ርዕሰ መስተዳድሩ በአርባምንጭ ከተማ የጋሞ አደባባይ በተመረቀበት ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፥ የአርባምንጭን የመስህብ ስፍራዎች በማብዛት የቱሪዝም መዳረሻነቷን ማጎልበት እንደሚገባ ገልጸዋል።
ከተማዋ በአርባዎቹ ምንጮቿ፣ በሕብረ ብሔራዊነቷ፣ በነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክ፣ በጋሞዎች የሰላምና አንድነት ባህል የምትታወቅ ናት ብለዋል።
ዛሬ የተመረቀው የጋሞ አደባባይ ደግሞ ተጨማሪ መገለጫዋና የውበት አክሊል እንደሆናት ጠቁመዋል።
በከተማዋ የተጀመሩ ለውጦችን ማፋጠን እንደሚገባም ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል።
አያይዘውም የከተማዋ ነዋሪ የ19ኛው የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል ተሳታፊ እንግዶችን በፍቅር ተቀብሎ ማስተናገድ እንደሚገባቸው አመላክተዋል።
የወል ትርክትን በማጠናከር ለሕብረ ብሔራዊ አንድነት መጎልበትና ለሀገር ብልፅግና ጉዞ መተባባር እንደሚገባም ተናግረዋል።