ቀጥታ፡

የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን መከበር ለአብሮነት፣ ለዘላቂ ሰላምና ልማት መሰረት የሚጥል ነው - አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር

አዲስ አበባ፤ ህዳር 26/2017(ኢዜአ)፦ የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን መከበር ለአብሮነት፣ ለዘላቂ ሰላምና ልማት መሰረት የሚጥል መሆኑን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ገለጹ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 19ኛውን የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን የማጠቃለያ መርሃ ግብር አካሂዷል።


 

በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን መከበሩ ህብረ ብሄራዊ አንድነትን በማጠናከር ጠንካራ ሀገረ መንግስት ለመገንባት ጥሩ መሰረት የሚያኖር መሆኑን ገልጸዋል። 

ከዚህ በፊት የቀኑን አከባበር ለሕብረ ብሔራዊ አንድነት ከመጠቀም አንጻር ክፍተት እንደነበር አስታውሰው አሁን ላይ ግን ለአብሮነት፣ ለዘላቂ ሰላምና ልማት መሰረት በሚሆን መልኩ እየተከበረ መሆኑን ተናግረዋል። 

በመሰረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት በመፍጠር ልዩነትን በውይይት በማጥበብ አሰባሳቢ የወል ትርክት መገንባት ይገባል ብለዋል።

በውይይት መግባባት፤ በመግባባት ደግሞ ህብረብሔራዊ አንድነትንና ብልጽግናን እውን ለማድረግ አስቻይ ሁኔታዎችን የሚፈጥር መሆኑን ጠቅሰዋል።

አዲስ አበባ የሁሉም አሻራ ያረፈባት፣ የሁሉም ሃሳብ የተካተተባት፣ የሁሉም ታሪክ የተጻፈባት የወል ቤታችንና ህብረብሔራዊነታችን ያደመቃት ከተማ መሆኗን ተናግረዋል።

በገበታ ለሀገር እና በኮሪደር ልማት በመዲናዋ የተከናወኑ እና እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎችም የኢትዮጵያን መፃኢ ተስፋ እና የብልጽግና ጉዞ የሚያሳዩ ናቸው ብለዋል። 


 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው፤ አዲስ አበባ ለህብረብሔራዊ ማንነት ማሳያ ትልቋ የኢትዮጵያውያን ቤት ናት ብለዋል። 

የከተማዋ ነዋሪዎች ትስሰር ያለበት፣ የመተሳሰብና የአብሮነት ማሳያ መሆኑን ጠቅሰው በቀጣይም ለከተማዋ እድገት በአብሮነት የልማት ጥረታችን ይቀጥላል ነው ያሉት።


 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ቡዜና አልከድር፤ በዓሉን ምክንያት በማድረግ ህብረብሔራዊ አንድነትን የሚያጠናክሩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።

አዲሱ ትውልድም የወል እውነታን በመገንዘብ በሚረከበው ሀገር ሊያበረክተው በሚችለው አስተዋጽኦ ላይ እንዲያተኩር የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።

በእለቱ የብሔር ብሔረሰቦችን ባህላዊ ምግብ የሚያሳይ አውደ ርእይም ተከፍቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም