በደብረ ማርቆስ ከተማ ሰላምን በዘላቂነት ለማስቀጠል ሚናችንን እናጠናክራለን - የሃይማኖት አባቶች - ኢዜአ አማርኛ
በደብረ ማርቆስ ከተማ ሰላምን በዘላቂነት ለማስቀጠል ሚናችንን እናጠናክራለን - የሃይማኖት አባቶች

ደብረ ማርቆስ፤ ህዳር 26/2017(ኢዜአ)፡- በደብረ ማርቆስ ከተማ የሰፈነውን ሰላም በዘላቂነት ለማስቀጠል ሚናቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የሃይማኖት አባቶች ገለጹ።
"ሰላም ለሀሉም ሁሉም ለሰላም" በሚል መሪ ሃሳብ በከተማው ዘላቂ ሰላም ለመገንባት በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ከሃይማኖት አባቶች ጋር የምክክር መድረክ ዛሬ በደብረማርቆስ ከተማ ተካሂዷል።
ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የደብረ ማርቆስ ከተማ ቤተክህነት ስራ አስኪያጅ ቆሞስ አባ ሃይለማሪያም ታገለ በሰጡት አስተያየት፤ ቤተክርስቲያኗ ስለ ሰላም አጥብቃ እያስተማረች እንደምትገኝ ተናግረዋል።
ያለ ሰላም የሚከወን ተግባር ባለመኖሩ ቤተክርስቲያን የማስተማርና የመስበክ ስራዋን አጠናክራ ትቀጥላለች ብለዋል።
የአስልምና እምነት ተከታይ ሸህ እንድሪስ መሀመድ በበኩላቸው፤ እንደ ሃይማኖት አባት የሰላምን አስፈላጊነት እያስተማሩ መሆኑን ገልጸዋል።
ዘላቂ ሰላምን በተሟላ መንገድ ለማስፈን ከንግግር ያለፈ ተግባር መፈጸም ያስፈልገናል ሲሉም አመልክተዋል።
በነበረው ችግር ከደረሰው ጉዳት በተግባር መማራቸውን የገለጹት ደግሞ የቃለ ህይወት ቤተክርስቲያን አገልጋይ ወንጌላዊ ዋለ አለሙ ናቸው።
የተገኘውን ሰላም ዘላቂ ለማድረግ እንደሚሰሩ አስታውቀዋል።
የደብረማርቆስ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ የፖለቲካ እና የአደረጃጀት ዘርፍ አማካሪ አቶ መልካሙ ሽባባው እንዳሉት፤ በከተማ አስተዳደሩ በነበረው ችግር ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳት ደርሷል።
ችግሩን ለመፍታት ሰላም ወዳዱን ህዝብ በማሳተፍ በተከናወነው የህግ ማስከበር ተግባር ሰላም ማስፈን መቻሉን ጠቅሰው፤ በዚህም የህዝብን ጥያቄ መሰረት ያደረጉ የልማት ስራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል።
ከዚህ በፊት በከተማ አስተዳደሩ በተካሄዱ ተደጋጋሚ የሰላም ውይይቶች ለሰፈነው ሰላም የጎላ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን አውስተዋል።
የሰፈነውን ሰላም ዘላቂ ለማድረግ እየተከናወነ ላለው ተግባር ውጤታማነት የሃይማኖት አባቶች በየእምነቶቻቸው ምዕምናኑን ስለሰላም በማስተማር እገዛቸውን ማጠናከር እንዳለባቸው ተናግረዋል።
በውይይት መድረኩ የተገኙት የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ የኔሰው መኮንን በበኩላቸው፤ ስለሰላም ማስተማር ከሁሉም የሚጠበቅ ተግባር ቢሆንም የሃይማኖት አባቶች ሚና ደግሞ የላቀ ነው ብለዋል።
ሀገር እንድትለማ ሁሉም ተከባብሮና ተቻችሎ እንዲኖር የሃይማኖት አባቶች ሚና የጎላ መሆኑን ገልጸው፤ ለዘላቂ ሰላም መስፈን ግንባር ቀደም ሆነው ማገዝ እንዳለባቸው አመልክተዋል።