በዓሉ በወል ጉዳዮች ላይ መግባባትን በመፍጠር ጠንካራ ሀገር ለመገንባት ወሳኝ ድርሻን እያበረከተ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በዓሉ በወል ጉዳዮች ላይ መግባባትን በመፍጠር ጠንካራ ሀገር ለመገንባት ወሳኝ ድርሻን እያበረከተ ነው
አርባ ምንጭ፣ ህዳር 26/2017 ( ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል በወል ጉዳዮች ላይ መግባባትን በመፍጠር ጠንካራ ሀገር ለመገንባት ወሳኝ ድርሻን እያበረከተ መሆኑ ተገለፀ።
የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓልን ምክንያት በማድረግ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በተገኙበት ሀገር አቀፍ የባህልና ቱሪዝም ባዛርና አውደ ርዕይ ዛሬ በአርባ ምንጭ ከተማ ተከፍቷል።
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ነፊሳ አልማሃዲ ባዛርና አውደ ርዕይ ላይ በተገኙበት ወቅት እንዳሉት የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ህገ መንግስታዊ ዋስትና የተረጋገጠበት እለት በመሆኑ ልዩ ያደርገዋል።
በተለይ በሀገራችን የሚገኙ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የሚሳተፉበት የጋራ መድረክ በመፍጠር ልምድና ተሞክሯቸውን እንዲለዋወጡ ጉልህ ሚና አለው ብለዋል።
እንዲሁም ባህላቸውንና ማህበራዊ አኗኗራቸውን በማሳየት ያለንን ብዝሃነት ጎልቶ እንዲወጣ ገንቢ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝም አስረድተዋል።
በዓሉ በተለይ በወል ጉዳዮች ላይ መግባባትን በመፍጠር ጠንካራ ሀገር ለመገንባት በሚደረገው እንቅስቃሴ ወሳኝ ድርሻ እያበረከተ መሆኑንም አመላክተዋል።
በዓሉ ለጋራ ፍትህ፣ ለዘላቂ ሰላም፣ ለነጻነትና ለዴሞክራሲ ሥርዓት መከበርና መረጋገጥ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ለማስቻል ገንቢ ሚና እንዳለውም አስረድተዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሰናይት ሰለሞን መሰል የአውደ ርእይ ዝግጅቶች ሁሉም ህዝቦች የእርስ በእርስ ተሞክሮ እንዲለዋወጡ ያስችላል ብለዋል።
በክልሉ እምቅ የሆነ ባህልና ቱውፊት አለ ያሉት ኃላፊዋ በዚህ ኤግዚቢሽን ይህንን በተጨባጭ ማሳየት የቻልንበት ነው ብለዋል።
ከልሉ አዲስ እንደ መሆኑ መጠን የፌዴሬሽን ምክር ቤት የዘንድሮውን በዓል እንድናከብር እድሉን ሲሰጠን ራሳችንን ለማስተዋወቅ እንደ መስተዋት ሆኖ እያገለገለ መሆኑን ተናግረዋል።
በነገው እለትም የብዝሀነት ቀንን በማስመልከት በዓሉን ለማክበር ከመላ ሀገሪቱ የሚመጡ ታዳሚዎችን በደማቅ ሥነ ሥርዓት የመቀበል መርሃ ግብር መሰናዳቱንም የቢሮ ኃላፊዋ አውስተዋል።