የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ ሕንጻ አዋጅን ጨምሮ የተለያዩ አዋጆችን መርምሮ አጸደቀ - ኢዜአ አማርኛ
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ ሕንጻ አዋጅን ጨምሮ የተለያዩ አዋጆችን መርምሮ አጸደቀ
አዲስ አበባ፤ ህዳር 26/2017(ኢዜአ)፦ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ ሕንጻ አዋጅን ጨምሮ የተለያዩ አዋጆችን መርምሮ አጸደቀ።
ምክር ቤቱ በዛሬው ዕለት 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 9ኛ መደበኛ ስብሰባውን ያካሄደ ሲሆን የተለያዩ አዋጆችን መርምሮ አጽድቋል።
ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ ሕንጻ ረቂቅ አዋጅ፣ የሪል ስቴት ልማትና የማይንቀሳቀስ ንብረት ግብይትና ግመታ ረቂቅ አዋጅ እንዲሁም የኤሌክትሮኒክስ ፊርማ ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቶ አጽድቋል።
ከሕንጻ አዋጁ ጋር በተያያዘም የምክር ቤቱ አባላት ትኩረት ይፈልጋሉ ባሏቸው ጉዳዮች ላይ ሀሳብና አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
በዚህም ሊፍት የሌላቸው ህንጻዎች፣ የህንጻ መጠቀሚያ ፈቃድ ሳይኖራቸው አገልግሎት የሚሰጡ አካላት ጉዳይ ትኩረት ይፈልጋል የሚሉ ሀሳቦችን አንስተዋል።
በተለይም ግንባታዎች ለአረንጓዴ ስፍራ በቂ ቦታ ያላቸው መሆኑ በሕንጻ አዋጁ በትኩረት መታየት እንዳለበት ጠቁመው በዚህ ረገድ ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ሊሰራ እንደሚገባም አመልክተዋል።
አካል ጉዳተኞችና ልዩ ድጋፍ የሚሹ ዜጎች የሚገጥማቸውን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችሉ አሰራሮችን መዘርጋትም እንዲሁ በትኩረት ሊታይ የሚገባው ጉዳይ መሆኑን አንስተዋል።
የምክር ቤቱ አባላት ከሪል ስቴት ልማት፣ የማይንቀሳቀስ ንብረት ግብይትና ግመታ ረቂቅ አዋጅ ጋር በተያያዘም ሊጤኑ ይገባል ያሏቸውን ጉዳዮች ጠቅሰዋል፡፡
ይህን ተከትሎ የገዥዎች መብት ጥበቃ ጉዳይ፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮችና ተያያዥ ጉዳዮችን በአጽንኦት ማየት እንደሚገባ አመልክተዋል።
በምክር ቤቱ የከተማ፣ መሠረተ ልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ እሸቱ ተመስገን (ዶ/ር) የአዋጆቹን ይዘት እና የውሳኔ ሀሳብ ያቀረቡ ሲሆን ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
እንደ ምክትል ሰብሳቢው ገለጻ የኢትዮጵያ ሕንጻ አዋጅ ግንባታዎች በጥራት፣ በጊዜ እና ሀብትን በሚቆጥብ መልኩ እንዲከናወኑ የሚያስችሉ አሰራሮችን ለመዘርጋት ያለመ ነው።
የሕንጻ ኮዶችና ስታንዳርዶች ሙሉ በሙሉ መተግበር ሌላው የአዋጁ ዓላማ መሆኑን ጠቅሰው የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመቀነስ ውጤታማ ሥራዎችን ለማከናወን አጋዥ መሆኑን አብራርተዋል።
ግንባታዎች አካል ጉዳተኞችንና ልዩ ድጋፍ የሚሹ ዜጎችን ታሳቢ ባደረገ መልኩ እንዲሰሩ አዋጁ ትኩረት መስጠቱንም ገልጸዋል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ ነባር ሕንጻዎች አካል ጉዳተኞችንና ልዩ ድጋፍ የሚሹ ዜጎችን በሚመጥን መልኩ የማስተካከያ ግንባታ እንዲያደርጉ የሚሰራበት መሆኑን ተናግረዋል።
የሕንጻ ዲዛይኖች ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመጠቀም እንዲዘጋጁ እንዲሁም ለዲዛይን ሥራ በቂ ጊዜ በመስጠት የግንባታ ጥራትን ማረጋገጥ ሌላው የአዋጁ ግብ መሆኑን አስረድተዋል።
የሪል ስቴት ልማትና የማይንቀሳቀስ ንብረት ግብይትና ግመታ ረቂቅ አዋጅን ይዘት ሲያብራሩም አዋጁ በኢትዮጵያ የቤት አቅርቦት ሥራዎችን ለማሳለጥ እና ለማሻሻል ታልሞ የተዘጋጀ መሆኑን ጠቁመዋል።
ዘርፉ በሕግና በስርዓት እንዲመራ ከማስቻሉም በላይ ወጥ የሆነ የግብይት ሥርዓት መዘርጋትም እንዲሁ በአዋጁ መካተቱን አብራርተዋል።
ለሪል ስቴት ግንባታዎች መሬት የሚቀርብበት ቅድመ ሁኔታ፣ መስፈርቶችና ማበረታቻዎች እንዲሁም የድጋፍና ክትትል ሥርዓቶችም በአጽንኦት የታዩ ጉዳዮች መሆናቸውን ተናግረዋል።
በአዋጁ መሰረት ከ80 በመቶ በላይ የተጠናቀቀ ቤት ማስተላለፍ የሚቻል ሲሆን የሚተላለፉ ቤቶች መሰረተ ልማት በአግባቡ የተሟላላቸው መሆን እንደሚገባቸው እሸቱ ተመስገን (ዶ/ር) አስታውቀዋል።
ግንባታው ከ 80 በመቶ በታች የሆነ ቤት ለገዥዎች ማስተላለፍ አይቻልም ያሉት ምክትል ሰብሳቢው ይህም የገዥዎችን መብት ለመጠበቅ አዋጁ ከያዛቸው ድንጋጌዎች መካከል የሚጠቀስ ነው ብለዋል።
ለግንባታ የሚያስፈልጉና ከውጭ የሚገቡ ግብዓቶችን በአገር ውስጥ መተካት ሌላው አዋጁ ከያዛቸው ጉዳዮች እንደሚካተት ጠቁመው ለዚህም የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው የሚሰሩበት አቅጣጫዎችን አዋጁ መያዙን ተናግረዋል።
ምክር ቤቱ በዛሬው ውሎው የኢትዮጵያ ሕንጻ ረቂቅ አዋጅ ቁጥር 1356/2017 ሆኖ በሙሉ ድምጽ ያጸደቀ ሲሆን የሪል ስቴት ልማትና የማይንቀሳቀስ ንብረት ግብይትና ግመታ ረቂቅ አዋጅ ቁጥር 1357 /2017ን ደግሞ በአብላጫ ድምጽ አጽድቋል።
በተመሳሳይም ምክር ቤቱ የኤሌክትሮኒክስ ፊርማ ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅንም መርምሮ አጽድቋል።