በክልሉ የዴሞክራሲ ተቋማት ሚናቸውን ይበልጥ እንዲያጠናክሩ የክልሉ መንግስት የበኩሉን ድጋፍ ሊያደርግ ይገባል - ቋሚ ኮሚቴው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የዴሞክራሲ ተቋማት ሚናቸውን ይበልጥ እንዲያጠናክሩ የክልሉ መንግስት የበኩሉን ድጋፍ ሊያደርግ ይገባል - ቋሚ ኮሚቴው
አሶሳ፤ ህዳር 26/2017(ኢዜአ)፦በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚገኙ የዴሞክራሲ ተቋማት ሚናቸውን ይበልጥ አጠናክረው እንዲቀጥሉ የክልሉ መንግስት የበኩሉን ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚገባ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።
ቋሚ ኮሚቴው በክልሉ የሚገኙ የዴሞክራሲ ተቋማትን የስራ እንቅስቃሴ ምልከታ እያደረገ ነው።
በቋሚ ኮሚቴው ምልከታ እየተደረገባቸው ካሉት የዴሞክራሲ ተቋማት መካከል የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እና የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፣ የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም፣ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን እና የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ቅርንጫፎች ይገኙበታል።
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል እና የቡድኑ አስተባባሪ ወይዘሮ አረጋሽ ተክሌ፤ ተቋማቱ የክልሉን ህዝብ እና መንግስት በማገልገል ሲወጡ የቆዩትን ሚና ይበልጥ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ድጋፍ እንደሚያሻቸው መረዳታቸውን ገልጸዋል።
እነዚህ የዴሞክራሲ ተቋማት ከዋናው መስሪያ ቤታቸው በተጨማሪ የክልሉ መንግስት በቁሳቁስ እና በሐሳብ ሊያግዟቸው እንደሚገባ ተናግረዋል።
በተለይም የመገናኛ ብዙሃን ተቋማቱ በሁሉም አካባቢዎች ተደራሽ እንዲሆኑ ያሉባቸውን የተሽከርካሪ እጥረት ለመፍታት የክልሉ መንግስት ተባባሪ እንዲሆን ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት አስተማማኝ የዜና ምንጭ በመሆን እያገለገለ መሆኑን እንደ አብነት ጠቅሰዋል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ አቶ መለሰ ኪዊ በበኩላቸው፤ ተቋማቱ በክልሉ እያከናወኑት ያለውን ተግባር ለማጠናከር የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል።
የዴሞክራሲ ተቋማቱ የዜጎችን መረጃ የማግኘት መብት የሚያጠናክሩ እንዲሁም የሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ የሚያደርጉትን ተግባር አጠናክረው እንዲቀጥሉ ምክትል አፈ ጉባኤው አሳስበዋል።
ከዴሞክራሲ ተቋማቱ ጋር በየጊዜው የምክክር መድረክ በማዘጋጀት ስራዎችን በጋራ ለማከናወን ዕቅድ መያዙንም ጠቁመዋል ።
ቋሚ ኮሚቴው በተቋማቱ ቅርንጫፎች የሚመለከታቸውን ጠንካራ እና መስተካከል ያለባቸውን ክፍተቶች ለዋናው መስሪያ ቤት እንደሚያቀርብ ተገልጿል።