ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን የከፍታ ጉዞ በቅብብሎሽ የሚያሳኩ ተተኪ አመራሮችን መፍጠር ይገባል-ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 26/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያን የከፍታ ጉዞ በቅብብሎሽ የሚያሳኩ ተተኪ አመራሮችን መፍጠር ይገባል ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ "ነጸብራቅ የመሪነት ኮንፍረንስ"ን በአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ አስጀምረዋል።


 

በመክፈቻ ንግግራቸውም ኢትዮጵያ ታላላቅ ድሎችን ያስመዘገቡ፣ የስልጣኔ ከፍታን የተቀዳጁ መሪዎች ሀገር ብትሆንም ያንን ማስቀጠል ባለመቻሉ ወደኋላ መቅረቷን ገልጸዋል።

በረዥሙ የሀገራችን ታሪክ ታላላቅ መሪዎች እንደነበሩ በማውሳት በአንድ ወቅት በርተው የጠፉና ሊደገሙ የማይችሉ አመራሮች ሆነዋል ሲሉም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ገናናነት የሚጠቀስባቸው ስኬቶች ከዘመን ዘመን መሸጋገርና መሳካት ያልቻሉት የአመራር ግንባታን እንደሀገር ባለማስቀጠላችን ነው ብለዋል።

አሁን ላይ ኢትዮጵያ የምትጠቀስባቸውን ጉድለቶች በመሙላት ወደ ከፍታ የማሻገር ጉዞ መጀመሩን ገልጸው የተተኪ አመራር ልማትም የዚሁ አካል መሆኑን ጠቅሰዋል።

ተተኪ ወጣት አመራሮችና ነባሩ አመራር የሚመክሩባቸውና ልምድ የሚለዋወጡባቸው መድረኮች ሲፈጠሩ በአመራር ትውልዶች መካከል መናበብ በመፍጠር ሀገራዊ ትልሞችን ለማሳካት ያስችላል ብለዋል።

በመሆኑም ኢትዮጵያ አመራሮች የምትፈጥርበት እንዲሁም በአመራሮች መካከል የትውልዳዊ ቅብብሎሸ ሥርዓት የምትገነባበት አሠራርና ተቋም እንደሚያስፈልጋት ተናግረዋል።

ይህ የተተኪም ሆነ የነባሩ አመራር ቁልፍ ተልዕኮ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

የሀገር ቀጣይነት ያለው ዕድገትም ሆነ ውድቀት የሐሳብ ጥራት፣ የአመራር ብቃት እና ቁርጠኝነት ላይ የተመሠረተ መሆኑን ጠቅሰው ችግሮችን ወደ ዕድል በመቀየር የሀገርን ዕድገት የሚያሳካ መሪ መሆን እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

ነፀብራቅ የመሪነት ኮንፍረንስ በኢትዮጵያ እና በአፍሪካ የተሣለጠ የትውልዶች አመራር ቅብብሎሽ የሚቀጥልበትን መንገድ የሚያሳይ ሊሆን ይገባል ብለዋል።

የተጀመሩ ሀገራዊ ኢኒሼቲቮችን በውጤታማነት በማስቀጠል የኢትዮጵያን የከፍታ ጉዞ ለማሳካት በትጋትና በብቃት የሚሠራ ተከታታይ አመራር በየዘመኑ ሲኖር መሆኑንም አፅኖት ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም