ቀጥታ፡

በበጀት ዓመቱ አራት ወራት ወደ ውጭ ከተላከ ቡና ከ674 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ ተገኘ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 26/2017(ኢዜአ)፦ በበጀት ዓመቱ አራት ወራት ወደ ውጭ ከተላከ ቡና ከ674 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን አስታወቀ።

የባለስልጣኑ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ሳህለማሪያም ገብረመድህን ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ባለፉት አራት ወራት 150 ሺህ 346 ቶን ቡና ለውጭ ገበያ መላኩን አስታውቀዋል፡፡

ተቋሙ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያዎቹ አራት ወራት 98 ሺህ 999 ቶን ቡና ለውጭ ገበያ ለመላክ ማቀዱን አስታውሰው የእቅዱን 152 በመቶ ማሳካት መቻሉን ተናግረዋል።

በዚህም 674 ነጥብ 55 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር በማስገባት የዕቅዱን 127 በመቶ ማሳካት መቻሉን ገልጸዋል፡፡

አፈጻጸሙ ከባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በመጠን 62 ሺህ 587 ቶን እና በገቢ 226 ነጥብ 89 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር፤ ወይም የ51 በመቶ ጭማሪ መመዝገቡን ተናግረዋል።

በተመሳሳይም በ2017 በጀት ዓመት ጥቅምት ወር 35 ሺህ 171 ቶን ቡና በመላክ 155 ነጥብ 53 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ገቢ መገኘቱን ጠቅሰዋል፡፡

አፈጻጸሙ ከባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ጊዜ ከተላከው ጋር ሲነጻጸር በመጠን 17 ሺህ 492 ቶን እና በገቢ 61 ነጥብ 91 ሚሊየን ዶላር ብልጫ እንዳለው ገልጸዋል፡፡

በ2017 በጀት ዓመት አራት ወራት የተላከው ቡና በመዳረሻ ሀገራት፣ በገቢና በመጠን ሲታይ ጀርመን፣ ሳዑዲ አረቢያና ቤልጂየም ቀዳሚ ሀገራት እንደነበሩ አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም