ቀጥታ፡

በቱሪስት መስህብ ሥፍራዎች ላይ እየተከናወነ ያለው ጥገና እና እድሳት የቱሪዝም ልማት ዘርፉን ኢኮኖሚያዊ አበርክቶ ያጎለብታል

ህዳር 26/2017(ኢዜአ)፦ የቱሪዝም ልማት ዘርፉን ለማነቃቃትና ለጎብኚዎች ምቹ ለማድረግ በተለያዩ አካባቢዎች በሚገኙ የቱሪስት መስህብ ሥፍራዎች እየተከናወነ ያለው ጥገና እና እድሳት የዘርፉን ኢኮኖሚያዊ አበርክቶ ለማጎልበት ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው ተገለፀ።

በየአካባቢው እየተከናወነ የሚገኘው የቱሪስት መስህብ ሥፍራዎች ጥገናና ዕድሳት ለዘርፉ መነቃቃት የራሳቸውን ድርሻ እያበረከቱ መሆናቸውም ተገልጿል።

በዓለማችን ከቱሪዝም ዘርፍ ቀዳሚ ተጠቃሚ ከሆኑት ሀገራት መካከል ፈረንሳይ፣ ስፔን፣ አሜሪካ፣ ቻይናና ህንድ ተጠቃሽ ናቸው።

እነዚህ ሀገራት ከሌሎች ዘርፎች ባልተናነሰ መልኩ ከቱሪዝም ዘርፍ በሚያገኙት ገቢ ኢኮኖሚያቸውን ይደግፋሉ።

ከተጠቀሱትም እንደ ቻይና ያሉ ሀገራት በሀገር ውስጥ ጎብኚዎች ብቻ ከዘርፉ የሚያገኙትን ገቢ ከዕለት ወደ ዕለት እያሳደጉ ከመሆናቸውም በላይ የውጭ ጎብኚዎችን ለመሳብ እያከናወኗቸው ያሉት ተግባራት በተሞክሮነት ሊወሰዱ የሚችሉ ናቸው።

ኢትዮጵያም በዓለም ቱሪዝም ድርጅት(WTO) እ.ኤ.አ በ2023 ባወጣው ሪፖርቱ በጥቅል የቱሪዝም ልማት የላቀ ውጤት ካስመዘገቡ 15 ሀገራት ጋር ቀዳሚ የሚል ደረጃን አግኝታለች።

ሪፖርቱ አክሎም በተጠቀሰው ዓመት ከጥር እስከ ሐምሌ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የቱሪስት ፍሰት የ28 በመቶ ዕድገት ማሳየቷን ጠቁሞ፤ በዚህም ከአፍሪካ የመጀመሪያውን ደረጃ እንዲሁም ከዓለም የሰባተኛ ደረጃ መያዟን ገልፆ ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በቱሪዝም እና ሆስፒታሊቲ አውደ ርዕይ ላይ ተገኝተው የቱሪዝም ዘርፍ በ10 ዓመቱ ዕቅድ ውስጥ እንዲካተት የተደረገበትን ዋነኛ ምክንያት ሲገልፁ ዘርፉ የተሰጠንን ፀጋ ማሳደግ የሚችል አቅምን ስለያዘ መሆኑን ማንሳታቸው የሚታወስ ነው።

ኢዜአ በአማራ፣ ሐረሪ እና በትግራይ ክልሎች የሚገኙ የቱሪስት መስህብ ስፍራዎች ጥገና እና እድሳት የዘርፉን አኮኖሚያዊ አበርክቶ ለማጎልበት በሚኖራቸው ሚና ዙሪያ ከሦስቱም ክልሎች የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ጋር ቆይታ አድርጓል።


 

በአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የቱሪዝም ልማት ዳይሬክተር አቶ መልካሙ አደም ለኢዜአ እንደገለጹት፣ የአማራ ክልል የፋሲል ግንብ፣ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፣ የሰሜን ተራሮችን ጨምሮ የበርካታ የቱሪስት መስህብ ሥፍራዎች መገኛ ነው።


 

በክልሉ ከሚገኙ በርካታ የቱሪስት መስህብ ሥፍራዎች መካከል አንዱ በሆነው የደቅ ደሴት የወደብ ግንባታ እየተከናወነ ሲሆን፤ ወደቡን የሚያገናኝ የመንገድ ግንባታም መጀመሩን ተናግረዋል።


 

በሐረሪ ክልል በቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ ላይ የተከናወኑ ሥራዎች የቱሪዝም ልማት ዘርፉን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ያሳድጋሉ ያሉት ደግሞ በክልሉ ባህል፣ ቅርስና ቱሪዝም ቢሮ የቅርስ ጥበቃ ዳይሪክተር አቶ አሚር ረመዳን ናቸው።

የጀጎል ዓለም አቀፍ ቅርስን ጨምሮ በክልሉ ከተማና ገጠር ወረዳዎች ለሚገኙ ታሪካዊና ጥንታዊ ቅርሶች የጥበቃና እንክብካቤ ሥራዎች ተሰርተዋል ብለዋል።


 

በትግራይ ክልል የሚገኙ የቱሪስት መስህብ ስፍራዎችን ለጎብኚዎች ምቹ ለማድረግ በክልሉ የተጀመሩ ጥረቶች እንዲጠናከሩ እየተደረገ መሆኑን የተናገሩት በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ዘነቡ ሐለፎም ናቸው።

በክልሉ ያሉ ታሪካዊ ስፍራዎችን ጠግኖ የቱሪስት ፍሰቱን ለማጎልበት በሚደረገው ጥረት ውስጥ የፌዴራል መንግስቱ ድጋፍ ከፍተኛ መሆኑንም ኃላፊዋ ጠቅሰዋል። 

በአማራ ክልል ተገንብተው የተጠናቀቁ የቱሪዝም መዳረሻዎች ጠቀሜታ የጎላ መሆኑን የገለፁት አቶ መልካሙ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ግንባታው ተጠናቅቆ  ወደ ስራ የገባው የጎርጎራ ሪዞርት ባህርዳርን ከጎንደር ጋር የሚያስተሳስር ድልድይ ሆኖ እያገለገለ እንደሆነ አመልክተዋል።

በደቡብ ወሎ ሃይቅ ላይ በገበታ ለትውልድ እየተገነባ የሚገኘው ፕሮጀክትም ከደብረ ብርሃን በደሴ አድርጎ ወደ ላሊበላ ለሚደረገው ጉብኝት ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥርም ተናግረዋል።

አቶ አሚር በበኩላቸው ለታሪካዊ ቅርሶቹና ለመስህብ ስፈራዎቹ እየተደረገ የሚገኘው ጥገና የጎብኚዎችን ፍሰት ለማሳደግ ዓይነተኛ ሚና እንዳለው ገልፀዋል።


 

በዚህም ለጀጎል አለም አቀፍ መግቢያ በሮች አንዱ የሆነው ሱጉጥ አጥ በሪ (ሰንጋ በር) እድሳት ተደርጎለት አገልግሎት እየሰጠ ሲሆን፣ አርጎባ በሪ (ኤረር በር) እና አሱሚይ በሪ (ፈላና በር) በመባል የሚታወቁ ታሪካዊ ሥፍራዎች ደግሞ እድሳት እየተደረገላቸው መሆኑን ተናግረዋል።

በክልሉ በአሁኑ ወቅት የፌዴራል ቅርስና ጥናት ባለስልጣን ታሪካዊ ሥፍራዎቹን ለመጠገን እያከናወነ የሚገኘው ተግባር የሚያስመሰግነው ነው ብለዋል።


 

ባለስልጣኑ በቅርቡ በአክሱም ሀውልት ቁጥር ሶስት ላይ ከጀመረው ጥናትና ጥገና በተጨማሪ የአቡነ አፍፄ እና የጊዮርጊስ ቕበፅያ ታሪካዊ ስፍራዎችን በተያዘው በጀት ዓመት ለመጠገን ማቀዱንም ተናግረዋል።

አለም አቀፉ የቱሪዝም ድርጅት መሰል አዎንታዊ ሪፖርቶች በሪፖርቱ ለተጠቀሱት ሀገራት የቱሪዝም ፍሰት መጨመር የሚኖረው አዎንታዊ ሚና አጠያያቂ አይደለም።

እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ሀገራትም ላሉባቸው እጥረቶች መፍትሄን በማበጀት ዘርፉን ለማነቃቃት እንዲንቀሳቀሱ ያደርጋቸዋል።

በዚህም መንግስት ዘርፉን ለማሳደግ የበለጠ ትኩረት ሰጥቶ እንዲንቀሳቀስ ዕድልን ይፈጥርለታል፤ የግል ባለሃብቶችም በዘርፉ ተሰማርተው ሰፊ የሥራ ዕድሎችን እንዲፈጥሩ መነሳሳትን ይፈጥራል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም