ቀጥታ፡

የተለያዩ አገራት ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ኢንቨስት የማድረግ ፍላጎት እያሳዩ ነው

አዲስ አበባ፤ ህዳር 26/2017(ኢዜአ)፦ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያን ተከትሎ የተለያዩ አገራት ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ኢንቨስት የማድረግ ፍላጎት እያሳዩ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል-አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው፤ በዲፕሎማሲው መስክ የተከናወኑ አበይት ጉዳዮች ላይ በማተኮር ሳምንታዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

በዚህም የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት አምባሳደር ታዬ አፅቀሥላሴ፤ አዲስ የተሾሙ የ24 አገራትን አምባሳደሮች የሹመት ደብዳቤ መቀበላቸውን አንስተዋል።

በኢትዮጵያ አሁን ላይ ኤምባሲያቸውን የከፈቱ አገራት ቁጥር 137 መድረሱን ጠቅሰው፤ ኮሎምቢያ በቅርቡ ለመክፈት በዝግጅት ላይ መሆኗን ተናግረዋል።

አዲስ አበባም የዲፕሎማሲ መዲናነቷና ተፈላጊነቷም እየጨመረ ለመምጣቱ ማረጋገጫ ነው ብለዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ(ዶ/ር) ከፈረንሳይ የአውሮፓ እና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጂን ኖኤል ባሮት ጋር ውይይት ማድረጋቸውንም አስታውሰዋል።

የኢትዮጵያ እና የፈረንሳይን አጋርነት ማጠናከር የሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ በማተኮር መወያየታቸውን ገልፀዋል።

በተለይም በትምህርት፣ ኢንቨስትመንት፣ የኃይል አቅርቦትና ሌሎችም መስኮች ይበልጥ ተቀራርበው የሚሰሩ መሆኑንም ተናግረዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር አሊ የሱፍ አሕመድ አል-ሻሪፍ ጋር መወያየታቸውንም ገልፀዋል።

ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን ባስጠበቀ መልኩ ለቀጣናው ሰላምና ደኅንነት በትኩረት እየሰራች መሆኑንም ጠቁመዋል።

በኢንቨስትመንትና ምጣኔ ኃብት ረገድም አበረታች ተግባራት መከናወናቸውን ጠቅሰው፤ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያን ተከትሎ የተለያዩ አገራት ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ኢንቨስት የማድረግ ፍላጎት እያሳዩ መሆኑን ተናግረዋል።

ኩባንያዎቹ በተለይም በግብርና፣ ማኑፋክቸሪንግ፣ ማዕድን፣ ቱሪዝም፣ አይሲቲ እና ሌሎችም ዘርፎች የመሰማራት ፍላጎት አሳይተዋል ነው ያሉት።

በዚህም ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ውስጥ ከዘጠኝ አገራት ከ20 በላይ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ የቅድመ ኢንቨስትመንት ጉብኝት ማድረጋቸውን አንስተዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ(ዶ/ር) ከእስያ መሠረተ-ልማት ኢንቨስትመንት ባንክ ፕሬዝዳንት ጂን ሊኩን ጋር በኢትዮጵያ እና በባንኩ መካከል ያለውን ትብብር ለማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ መምከራቸውንም ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም