ሀገር አቀፍ የባህልና ቱሪዝም ባዛርና አውደ ርዕይ በአርባ ምንጭ ከተማ ተከፈተ - ኢዜአ አማርኛ
ሀገር አቀፍ የባህልና ቱሪዝም ባዛርና አውደ ርዕይ በአርባ ምንጭ ከተማ ተከፈተ
አርባ ምንጭ፤ ህዳር 26/2017(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓልን ምክንያት በማድረግ ሀገር አቀፍ የባህልና ቱሪዝም ባዛርና አውደ ርዕይ በአርባ ምንጭ ከተማ ተከፈተ።
ለበዓሉ የተዘጋጀውን ባዛርና አውደ ርዕይ ዛሬ የከፈቱት የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ነፊሳ አልማሀዲ እና የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ ናቸው።
በዝግጅቱ ላይ በባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ የተመራና ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ሃላፊዎችን ያካተተ ቡድንም ተገኝቷል።
በዓሉ "ሀገራዊ መግባባት ለህብረ ብሔራዊ አንድነት" በሚል መሪ ሀሳብ ከህዳር 25 ቀን 2017 ጀምሮ በአርባ ምንጭ ከተማ በተለያዩ ዝግጅቶች በድምቀት እየተከበረ ነው።
በባዛርና አውደ ርዕዩ ላይ በክልሉ የሚገኙ የተለያዩ ብሔሮችና ብሔረሰቦች መገለጫ የሆኑ የባህል ውጤቶች ለእይታ ቀርበዋል።
በዓሉ ከትናንት ጀምሮ በተለያዩ ስያሜዎች እየተከበረ ሲሆን የዛሬው ባዛርና አውደ ርዕይም "የደቡብ ኢትዮጵያ ቀን" አካል መሆኑ ተገልጿል።
ትናንት የበዓሉ ማስጀመሪያ በሆነው "የወንድማማችነት ቀን" የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደን ጨምሮ ከ10 ሺህ በላይ ሯጮች የተሳተፉበት የአምስት ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር መካሄዱ ይታወሳል።
ዛሬም በጋሞ ባህል ማዕከል የተዘጋጀው ባዛርና አውደ ርዕይ ለህዝብ ክፍት ሆኖ እየተጎበኘ ነው።
በባዛሩ ላይ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ባህላዊ አልባሳትና ምግቦችን እያስተዋወቁ ይገኛሉ።
የዘንድሮው የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል በሀገር አቀፍ ደረጃ በመጪው እሁድ በአርባ ምንጭ ከተማ በተለያዩ ሁነቶች በድምቀት ይከበራል።