ቀጥታ፡

የሳዑዲ አረቢያ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በተለያዩ መስኮች መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ጠንካራ ፍላጎት እንዳላቸው ገለጹ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 26/2017(ኢዜአ)፦ የሳዑዲ አረቢያ ባለሀብቶች ግብርናና ማዕድንን ጨምሮ በኢትዮጵያ በተለያዩ መስኮች መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ጠንካራ ፍላጎት እንዳላቸው ገለጹ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ከሳዑዲ አረቢያ ባለሀብቶች ጋር በሪያድ ተወያይተዋል።

ውይይቱ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት እድሎች ላይ ያተኮረ መሆኑ ተገልጿል።

አምባሳደር ምስጋኑ ኢትዮጵያ በቅርቡ የወጪ ንግድ እና ኢንቨስትመንትን ማሻሻል አላማ በማድረግ እያከናወነች ያለውን የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች አስመልክቶ ገለጻ አድርገዋል።

ማሻሻያዎቹ በተለያዩ መስኮች ለዓለም አቀፍ ኢንቨስተሮች ምቹ ምህዳር መፍጠሩን አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ በፍጥነት እያደገ እና እየሰፋ ያለ ኢኮኖሚ፣ ወጣትና መለወጥ የሚችል የሰው ኃይል እንዲሁም ከ120 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ እንዳላት ገልጸዋል።


 

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ስትራቴጂካዊ ስፍራ እንደምትገኝና ይህም በግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በማዕድንና የአገልግሎት ዘርፎች ልዩ እድሎች መያዟን ተናግረዋል።

የሳዑዲ አረቢያ ባለሀብቶች እና የኩባንያ ኃላፊዎች ለቀረበላቸው ገለጻ እና ለነበረው ውይይት ምስጋና አቅርበው በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት መስክ ለመሰማራት ጠንካራ ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል።

የግብርና ምርት፣ የእንስሳት እርባታ፣ ማዕድን እና ቱሪዝም በተለያዩ መስኮች በትብብር መስራት በሚቻልባቸው መስኮች ላይ ሀሳባቸውን አንስተዋል።

ባለሀብቶቹ በኢትዮጵያ ኩባንያዎችን በማቋቋም በአፍሪካ ሰፊ ገበያ ለማግኘት ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል።

ውይይቱ የኢትዮጵያ እና ሳዑዲ አረቢያ የኢኮኖሚ ትስስርን ማጠናከር የሚያስችል መሆኑ ተገልጿል።

ምክክሩ ኢትዮጵያ ለውጭ ባለሀብቶች ምቹ የስራ ከባቢ አየር ለመፍጠር ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም