ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ዘላቂ የከተማ ልማትን እውን ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች ውጤት እያስገኙ ነው

አዲስ አበባ፤ ህዳር 25/2017(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ዘላቂ የከተማ ልማትን እውን ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች ውጤት እያስገኙ መሆናቸውን የከተማ እና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ፈንታ ደጀን ገለጹ።

ሁለተኛው የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ ሰፈራ መርሃ ግብር(UN-Habitat) የስራ አመራር ቦርድ መደበኛ ስብሰባ ዛሬ በኬንያ ናይሮቢ ተጀምሯል።

በስብሰባው ላይ የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ፈንታ ደጀን እና በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ባጫ ደበሌ ተሳትፈዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው በስብሰባው ላይ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) አመራር ሰጪነት በኢትዮጵያ ዘላቂ እና የማይበገር የከተማ ልማት ለመፍጠር እየተከናወኑ ያሉ ኢኒሼቲቮችን አንስተዋል።

አቶ ፈንታ የማይበገር የከተማ እንቅስቃሴን የሚያሳልጡ የከተማ የአረንጓዴ መተላለፊያ ኮሪደሮች ልማትን አስመልክቶ ገለጻ አድርገዋል።

ለእግረኞች የሚስማሙ መተላለፊያ መንገዶች፣ የብስክሌት መንገዶች እና ዘመናዊ የመንገድ መሰረተ ልማቶች እየተገነቡ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ሕዝብን ማዕከል ያደረጉ የስማርት ከተሞችን በማስፋት እና የዲጂታል አማራጮችን በመጠቀም የአገልግሎት አሰጣጥ እና የከተማ አስተዳደርን ለማሻሻል እየተሰራ ነው ብለዋል።

በተጨማሪም ሚኒስትር ዴኤታው በኢትዮጵያ ስለተካሄደው የመጀመሪያው የአፍሪካ ከተማ ፎረም ተሳታፊዎች ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን ፎረሙ በቀጣናው እና በተቀረው ዓለም ያለውን የከተሜነት ፈተናዎች ምላሽ መስጠት የሚያስችሉ ቁልፍ ውሳኔዎች የተላለፉበት እንደሆነ አውስተዋል።

ሁሉም አጋር አካላት የአዲስ አበባ የውሳኔ ሀሳብ(Addis Ababa Declaration) ጨምሮ በፎረሙ የተላለፉ የውሳኔ ሀሳቦች ትግበራን እንዲደግፉ ጥሪ አቅርበዋል።

የውሳኔ ሀሳቡ ለዘላቂ ከተማ ልማት ወሳኝ በሆኑ የአቅም ግንባታ፣ የእውቀት ሽግግር፣ የሀብት ማሰባሰብ እና የፖሊሲ ተጣጣሚነት ላይ ያተኮሩ ናቸው።

ሁለተኛው የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ ሰፈራ መርሃ ግብር(UN-Habitat) የስራ አመራር ቦርድ መደበኛ ስብሰባ ህዳር 27 ቀን 2017 ዓ.ም እንደሚቆይ በኬንያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም