በሴቶች ላይ የሚደርሱ ፆታዊ ጥቃቶችን ከመከላከል ባሻገር ለስነ ልቦናና ለህግ ድጋፍ ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ ተገለፀ

ቦንጋ፤ ህዳር 25/2017(ኢዜአ)፦ በሴቶች ላይ የሚደርሱ ፆታዊ ጥቃቶችን ከመከላከል ባሻገር ለስነ ልቦናና ለህግ ማማከር ድጋፍ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ፀሐይ ደርጫ አሳሰቡ።

ቢሮው በሴት ልጅ ግርዛትና ያለ ዕድሜ ጋብቻ ላይ የማህበረሰቡን ግንዛቤ በማሳደግ የስነ-ልቦናና የህግ ማማከር አገልግሎቶች ላይ ያተኮረ ስልጠና ለባለድርሻ አካላት ሰጥቷል።


 

በመድረኩ ላይ የተገኙት የክልሉ ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ፀሐይ ደርጫ እንዳሉት በሴቶች ላይ የሚደርሱ ፆታዊ ጥቃቶች እንዳይፈፀሙ ከመከላከል ባሻገር ለስነ-ልቦናና ለህግ ማማከር አገልግሎቶች ትኩረት መስጠት ወሳኝ ነው።

ምክር ቤቱም ከቢሮው ጋር በመቀናጀት ጠንካራ የአሰራር ስርዓቶችን በማበጀትና ተጠያቂነትን በማስፈን ላይ እየሰራ በመሆኑ የማህበረሰቡ ግንዛቤ እየሰፋ በመምጣቱ ውጤት እየተመዘገበ መሆኑንም ገልፀዋል።

በሴቶች ላይ የሚደርሱ ፆታዊ ጥቃቶችና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች የሚያስከትሉት ስነ-ልቦናዊና ማህበራዊ ጫናዎች ከፍተኛ በመሆናቸው ስራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ አሳስበዋል ።

ለሴቶች የስነልቦና ድጋፍና እንክብካቤ በማድረግ ማህበራዊ፣ ስነልቦናዊና አካላዊ ጉዳቶችን መቀነስ ላይ በተቀናጀ መልኩ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሪት ለምለም አምሳሉ ተናግረዋል።

የሀይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችንና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችን በማቀፍ የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራዎች በመሰራታቸው በርካታ ቀበሌዎች ከፆታ ጥቃትና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ነፃ እንዲሆኑ ማድረግ መቻሉን ጠቁመዋል።

በአካባቢያቸው ከዚህ ቀደም የሴት ልጅ ግርዛትና ያለ እድሜ ጋብቻ በሰፊው ይፈፀም እንደነበረ የገለፁት ከካፋ ዞን ዴቻ ወረዳ የመድረኩ ተሳታፊ ወይዘሮ አረጉ ሀይሌ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በተቀናጀ አግባብ በተሰሩ ስራዎች መቀነሱን ተናግረዋል።

በሴቶች ላይ ጥቃት ሲደርስ መብቷን እንድታስጠብቅ የተለያዩ አደረጃጀቶችን በማጠናከር ትምህርት እየተሰጠ መሆኑን ጠቁመው፣ በወሰዱት ስልጠና ታግዘው ለተሻለ ውጤት እንደሚተጉም ገልፀዋል።

የዳውሮ ዞን እሰራ ወረዳ ሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ጽህፈት ቤት ባለሙያ አቶ አባተ አበራ በበኩላቸው በወረዳቸው በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ ፆታዊ ጥቃቶችንና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለመከላከል የሚያስችል የግንዛቤ ማስጨበጥና የህግ ተጠያቂነትን ለማስፈን እየሰሩ መሆኑን ገልፀዋል።

በወረዳው የሴት ልጅ ግርዛት፣ ያለ እድሜ ጋብቻ እና ጠለፋን ለመከላከል በተሰጡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች የህብረተሰቡ አስተሳሰብ እየተለወጠ በመምጣቱ ድርጊቱ እየቀነሰ መምጣቱን ተናግረዋል።

በመድረኩ በስነ-ልቦናና በማህበራዊ ድጋፍ አሰጣጥ ዙሪያ የተዘጋጀ ሰነድ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም