ቀጥታ፡

ጎንደር በፈጣን ለውጥ ላይ የምትገኝ ሰላማዊ ከተማ መሆኗን ተመልክተናል - የሲዳማና የአፋር ክልሎች ምክር ቤቶች አፈ ጉባኤዎች

አዲስ አበባ፤ ህዳር 25/2017(ኢዜአ):- ጎንደር በፈጣን ለውጥ ላይ የምትገኝ ሰላማዊ ከተማ መሆኗን የሲዳማና የአፋር ክልሎች ምክር ቤቶች አፈ ጉባኤዎች ገለጹ።

19ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን "ሀገራዊ መግባባት ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት" በሚል መሪ ሀሳብ በአማራ ክልል ደረጃ በጎንደር ከተማ ተከብሯል።

በበዓሉ ላይ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር፣ የተለያዩ ክልሎች ምክር ቤት አፈ ጉባኤዎችና ሌሎች የመንግሥት የሥራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።

የበዓሉ ተሳታፊዎች የጎንደር የኮሪደር ልማት እና የአፄ ፋሲል ግንብ የእድሳት ሥራን ጎብኝተዋል።

የሲዳማ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፋንታዬ ከበደ፥ ጎንደርን ከጠበቋት በላይ ውብ እና ታሪካዊ ከተማ ሆና  እንዳገኟት ተናግረዋል።


 

የጎንደር ከተማ የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች መገኛ መሆኗን በማንሳት፥ የከተማዋ ነዋሪ በፍቅርና በአንድነት የሚኖር መሆኑን በጉብኝቴ አይቻለሁ ብለዋል።

የአፋር ክልል ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አስያ ከማል በበኩላቸው፣ ጎንደር ከተማ የኢትዮጵያውያን የታሪክ ማዕከል መሆኗን ገልጸዋል።

ጎንደር ከተማ በሩቅ ከሚወራው በተቃራኒ ፍጹም ሰላማዊና በፈጣን ልማት ላይ መሆኗን በአካል ተገኝቼ አረጋግጫለሁ ብለዋል።

የጎንደር ህዝብ የሰላምን ዋጋ ጠንቅቆ የሚያውቅ ነው ያሉት አፈ ጉባኤዎቹ፥ የኮሪደር ልማትን ጨምሮ በከተማዋ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎችን በመደገፍና በማገዝ አርዓያ መሆናቸውን ተናግረዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም