ቀጥታ፡

በድሬዳዋ ገጠር ቀበሌዎች እየተከናወኑ የሚገኙ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያግዙ ናቸው

ድሬዳዋ፤ ህዳር 25/2017(ኢዜአ)፦ በድሬዳዋ ገጠር ቀበሌዎች እየተከናወኑ የሚገኙ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚደረጉ ጥረቶችን የሚያግዙ መሆናቸውን በዓለም ባንክ የኢትዮጵያ፣ የደቡብ ሱዳን፣ የኤርትራ፣ እና የሱዳን ዋና ዳይሬክተር መርየም ሳሊም ተናገሩ።

በዳይሬክተሯ የሚመራው የዓለም ባንክ ከፍተኛ የአመራር አባላት ቡድን በዓለም ባንክ ድጋፍና በመንግስት ጥምረት እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ስራዎችን በድሬዳዋ ገጠር ቀበሌዎች ዛሬ ተመልክቷል።

ከጉብኝቱ በኋላ ከድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ እና ከአስተዳደሩ የግብርና፣ ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ አመራር አባላት ጋር በገጠር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እየተከናወኑ በሚገኙ ተግባራት ለውጦች ላይ መክረዋል።

በወቅቱም ዳይሬክተሯ መርየም ሳሊም ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በድሬዳዋ ገጠር ቀበሌዎች እየተከናወኑ የሚገኙ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራዎች የሚበረታቱ ናቸው።

''ዛሬ በድሬደዋ ሁላንሁሉል ገጠር ቀበሌ የተመለከትነው የአፈርና ውሃ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራዎች ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ማህበረሰብ ለመፍጠር የተጀመሩ ጥረቶችን የሚያሳኩ ናቸው'' ብለዋል።

በአካባቢው የተፈጥሮ ሃብትን በአግባቡ በመጠበቅ እና በመጠቀም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተጀመሩት ስራዎች ተስፋ ሰጪ መሆናቸውን ገልጸዋል ።

የድሬዳዋ አስተዳደር የግብርና ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ አቶ ኑረዲን አብደላ በበኩላቸው በአካባቢው የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በተሰሩ ስራዎች መደሰታቸውን ተናግረዋል።

በድሬዳዋና ገጠር ቀበሌዎች የአነስተኛ መስኖ እና የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ጭምር ተገንብተው ከ64ሺ በላይ ነዋሪዎች በተለያዩ የመስኖ ስራዎች ላይ ተጠቃሚ በመሆን ላይ ይገኛሉ ብለዋል።

እነዚህ ስራዎች ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ልማት መርሃ ግብርን ዕውን በማድረግ በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ ግብን እያሳኩ መሆናቸውን አቶ ኑረዲን ተናግረዋል።

የልዑካን ቡድኑ ከድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር ጋር የተወያዩ ሲሆን ከንቲባው የገጠሩን ህብረተሰብ ከተረጂነት ወደ አምራችነት ለማሸጋገር የተቀናጁ የልማት ስራዎችን በ38 የገጠር ቀበሌዎች እየተከናወኑ መሆኑን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም