በሶማሌ ክልል ከተሞች ለነዋሪዎቻቸው የተመቹና የተቀላጠፈ ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶች መስጠት የሚያስችል አቅም እንዲፈጥሩ እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በሶማሌ ክልል ከተሞች ለነዋሪዎቻቸው የተመቹና የተቀላጠፈ ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶች መስጠት የሚያስችል አቅም እንዲፈጥሩ እየተደረገ ነው
ጅግጅጋ፤ ህዳር 25/2017(ኢዜአ):- በሶማሌ ክልል ከተሞች ለነዋሪዎቻቸው የተመቹና የተቀላጠፈ ማዘጋጃቤታዊ አገልግሎቶችን መስጠት የሚያስችል አቅም እንዲፈጥሩ እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ከተማና ኮንስትራክሽን ቢሮ ገለጸ።
ቢሮው ከኢትዮጵያ ከተሞች የትብብር መድረክ ጋር በመተባበር ለከንቲባዎች፣ ለከተማ አስተዳደር ማዘጋጃ ቤት ስራ አስኪያጆችና ባለሙያዎች ያዘጋጀው የልምድ ልውውጥ መድረክ በጅግጅጋ ከተማ ተካሂዷል።
የክልሉ ከተማና ኮንስትራክሽን ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ጣይብ አህመድ በመድረኩ ላይ እንደተናገሩት በክልሉ ከተሞች በፍጥነት እየተስፋፉ ነው።
የከተሞችን መስፋፋት ተከትሎ የህዝቡን የአገልግሎት አሰጣጥ እንዲሁም የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች ዘላቂ ልማትን ታሳቢ ባደረገ መልኩ እንዲከናወኑ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
ከተሞች ለነዋሪዎቻቸው የተመቹና የተቀላጠፈ ማዘጋጃቤታዊ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ ልዩ ልዩ መመሪያዎችና የልምድ ልውውጥ መድረኮች እንዲያገኙ መደረጉን አንስተዋል።
የከተሞች ገቢ አሰባሰብ አቅምን ለማሳደግ ትልቅ ተኩረት መሰጠቱን ጠቅሰው ቢሮው በቅርቡ ባካሄደው መነሻ ጥናት በክልሉ በማዘጋጃ ቤት ደረጃ አገልግሎት የሚሰጡ ከአንድ መቶ በላይ ከተሞች ከ400 ሚልየን ብር በላይ ገቢ እንደሚሰበሰብ መለየቱን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ከተሞች የትብብር መድረክ ዋና ዳይሬክተር ተወካይ አቶ ዘገየ ሀብትዬ ባለፈው ዓመት 25 የሚሆኑ የትብብር መድረኩ አባል ከተማ ከንቲባዎች በአውሮፓ፣ በአፍሪካ፣ በላቲን አሜሪካ፣ በሰሜን አሜሪካና በእስያ ጉብኝት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
የትብብር መድረኩ በያዝነው ዓመት 102 አባል እና እጩ ከተሞች የሚሳተፉበት የተለያዩ አውደ ጥናቶች፣ ወርክ ሾፖች፣ ልምድ ልውውጥ መድረኮችን በማዘጋጀት እንዲሁም ከንቲባዎችንና የማዘጋጃ ቤት ስራ አስኪያጆችን በከተማ ልማትና በመልካም አስተዳደር ዙሪያ እርስ በርስ እንዲማማሩ ያደረጋል ብለዋል።
መድረኩ ከንቲባዎችን በውጭ ሀገር የሚገኙ መልካም ተሞክሮዎችን እንዲቀስሙና እንዲጎበኙ በማድረግ እንዲሁም ስልጠና የሚያገኙበትን መንገድ በማመቻቸት ልምዳቸውን እንዲያዳብሩ እያደረገ ይገኛል ነው ያሉት፡፡
የኢትዮጵያ ከተሞች የትብብር መድረክ ዋና ተግባር የከተሞችን ልማት በሚመለከት የመማሪያ፣ የእውቀት ሽግግርና የመግባቢያ መድረክ መፍጠር መሆኑ ተጠቁሟል።