ቀጥታ፡

የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል በሰላም እንዲከበር አስፈላጊው ዝግጅት መጠናቀቁ ተገለጸ

አርባምንጭ ፤ ህዳር 25/2017(ኢዜአ)፡- 19ኛው የኢትዮጵያ የብሔሮች፣  ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል በሰላም እንዲከበር አስፈላጊ ዝግጅት መጠናቀቁን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ አስታወቀ።

19ኛው የኢትዮጵያ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን "ሀገራዊ መግባባት ለህብረ ብሔራዊ አንድነት" በሚል መሪ ሀሳብ ህዳር 29/2017 ዓ/ም በአርባምንጭ ከተማ ይከበራል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ሃላፊ አቶ ወገኔ ብዙነህና የፌዴሬሽን ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ምክትል ሃላፊ አቶ በላይ ወድሻ በዓሉን በማስመልከት ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል።

የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ሃላፊ አቶ ወገኔ ብዙነህ፤ በዓሉ በሰላም እንዲከበር አስፈላጊው ዝግጅት ተጠናቋል ብለዋል።

ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክልሎች የሚመጡ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ልዑካን ቡድን ያለ ምንም ስጋት በዓሉን እንዲያከብሩ የፌዴራልና የክልሉ የሰላም ጥምር ኮሚቴ ዝግጅት ሲያደርግ ቆይቷል ነው ያሉት።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ምክትል ሃላፊ አቶ በላይ ወድሻ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል አንድነትና አብሮነት እንዲጠናከር ልዩ አንደምታ አለው ብለዋል።

እንግዶቹ ያለምንም ስጋት በዓሉን እንዲያከብሩ የተዋቀረው የሰላምና የደህንነት ኮሚቴ በቂ ዝግጅት አድርጓል ሲሉም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም