ኢንስቲትዩቱ በክልሉ ለሚገኙ የገበሬዎች የብድርና ቁጠባ ህብረት ሥራ ማህበራት ከ41 ሚሊዮን ብር በላይ የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ኢንስቲትዩቱ በክልሉ ለሚገኙ የገበሬዎች የብድርና ቁጠባ ህብረት ሥራ ማህበራት ከ41 ሚሊዮን ብር በላይ የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ
መቀሌ፤ ህዳር 25/2017(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት በትግራይ ለሚገኙ የገበሬዎች የብድርና ቁጠባ ህብረት ስራ ማህበራት ከ41 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የኤሌክትሮኒክስ ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን አስታወቀ።
በኢንሰቲትዩቱ የትግራይ ክልል ቅርንጫፍ ኃላፊ አብረሃ ኪዳነማርያም (ዶ/ር) እንደገለፁት፡ የተደረገው ድጋፍ በትግራይ ክልል የሚገኙ የገጠር የገበሬዎች የህብረት ስራ ማህበራትን ለማጠናከር ያግዛል።
የተደረገው ድጋፍ 280 ዴስክቶፕ ኮምፒዩውተሮች እና 280 ፕሪንተርን ጨምሮ ለዲጂታላይዜሽን አገልግሎት የሚውሉ ከ41 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው ቁሳቁስ መሆናቸውን ገልፀዋል።
አርሶ አደሩ በየቀበሌው የእርሻ ግብዓቶችን በቀላሉ እንዲያገኝ እና በህብረት ስራ ማህበራቱ በቴክኖሎጂ የታገዘ የዲጂታል አገልግሎትን ተግባራዊ ለማድረግ በማለም የተደረገ ድጋፍ መሆኑንም ኃላፊው ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ባለፉት ሁለት ዓመታት ለህብረት ስራ ማህበራቱ 71 ሚሊዮን ብር የሚገመት ድጋፍ ማድረጉንም ገልፀዋል።
በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የህብረት ስራ ማህበራት ማስፋፊያ እና የገበያ ልማት ኤጀንሲ ኃላፊ አቶ ነጋ አሰፋ በበኩላቸው፤ የተደረገው ድጋፍ ማህበራቱን በማጠናከር ከተለመደው አካሄድ ወጥተው ዘመናዊ አሰራርን ለመዘርጋት ያግዛል ብለዋል።