ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አጀንዳዎችን ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስረከበ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 25/2017(ኢዜአ):- የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በክልላዊና ሀገራዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሰብስበው የቀረቡ አጀንዳዎችን ለኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስረከበ።

የፖለቲካ ፓርቲዎቹን አጀንዳም የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን አየለ እና የስራ አስፈጻሚ አባላት ለሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ የስራ ሃላፊዎች አስረክበዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ያስረከቡት አጀንዳም ከሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች የተሰበሰቡና ወሳኝ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ መሆናቸው ተጠቁሟል።

በኢትዮጵያ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት ሚናቸውን ሲወጡ መቆየታቸውም በዚሁ ወቅት ተነስቷል።

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን አየለ፤ ምክር ቤቱ ለሀገራዊ ምክክሩ ዕውን መሆን የበኩሉን እየተወጣ ይገኛል ብለዋል።


 

በቀጣይነትም ምክር ቤቱ ለኢትዮጵያ ልማት፣ ሰላምና ዴሞክራሲ መረጋገጥ የበኩሉን ይወጣል ሲሉም ተናግረዋል።

አጀንጃዎቹም ከሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች የተሰበሰቡ መሆናቸውን ጠቁመው በጠቅላላ ጉባኤም የጸደቁ ናቸው ብለዋል።

አጀንዳዎቹ በሰባት ዋና ዋና ክፍሎች እና በ64 ዝርዝር ጉዳዮች የተጠናከሩ ስለመሆናቸውም አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት፣ ለልማት፣ ለሰላምና ዴሞክራሲ መጎልበት ሚናውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ፤ ለኮሚሽኑ ተባባሪ የሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለምክክሩ ስኬታማነት የበኩላቸውን ሚና በመወጣት ላይ ይገኛሉ ብለዋል፡፡


 

ኮሚሽኑ በተቋማትና በማህበረሰብ ክፍሎች ተደራጅተው የሚቀርቡ አጀንዳዎችን በአግባቡ እንደሚጠቀምባቸውም ጠቁመዋል፡፡

ዋና ኮሚሽነሩ ከታህሳስ 5 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ በኦሮሚያ ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብ ስራ እንደሚጀመርም ተናግረዋል፡፡

በዚህም ለዋናው የምክክር ሂደት ተሳታፊ የሚሆኑ ባለድርሻ አካላት እንደሚመረጡ ገልጸዋል።

በትግራይ እና በአማራ ክልሎች ሂደቱን የማከናወን ስራ ለመጀመር እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም