ቀጥታ፡

አዲሱ የግብርና እና ገጠር ልማት ፖሊሲ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እና የመስኖ ልማት ስራውን ለማሳደግ ሰፊ አስተዋጽኦ ያበረክታል

አዲስ አበባ፤ ህዳር 25/2017(ኢዜአ):- አዲሱ የግብርና እና ገጠር ልማት ፖሊሲ የምግብ ሉዓላዊነትን ከማረጋገጥ ባለፈ የመስኖ ልማት ስራውን ለማሳደግ ሰፊ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ገለፀ።

ፖሊሲው በገጠር መዋቅራዊ ለውጥ ለማምጣት እንደሚያግዝም ተገልጿል።

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ማንደፍሮ ንጉሴ(ዶ/ር) አዲሱ የግብርና እና ገጠር ልማት ፖሊሲን አስመልክቶ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

አዲሱ የግብርና እና ገጠር ልማት ፖሊሲ የአርሶ አደሩንና አርብቶ አደሩን የኑሮ ሁኔታ ትርጉም ባለው መልኩ መለወጥ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

በፖሊሲው አርሶና አርብቶ አደሩ ግብዓቶችን ለመግዛት የሚገጥመውን ችግር ለመቋቋም በቂ የብድር አገልግሎት እንዲያገኝ የሚያስችል ነው ብለዋል።

በዋነኛነትም አርሶ አደሩ ባለው ንብረት፣ በመሬቱ፣ በቋሚ ተክሉ እና እንስሳቶቹ ብድር እንዲያገኝ እንደሚያስችልም ገልጸዋል።

ይህም ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ በሀገርም ሆነ በቤተሰብ ደረጃ ከፍተኛ ለውጥ ማምጣት የሚያስችል መሆኑን ጠቅሰዋል።

ፖሊሲው በዘርፉ ያለውን የምርምር አቅም እንደሚያሳድገው ገልጸው የሀገሪቱ የመስኖ ልማት ስራንም ውጤታማ ማድረግ ያስችላል ነው ያሉት።

ፖሊሲው የግብርና ዘርፉን ለማሳደግ ከሚያበረክተው አስተዋጽኦ ባሻገር በገጠሩ አካባቢ የመሰረተ ልማት እድገት እንዲኖር እንደሚያስችል አንስተዋል።

በተጨማሪም ከግብርናው ጋር ተያይዘው የሚከናወኑ የልማት ስራዎችን ለማሻሻል እንደሚረዳም ነው ያስረዱት።

ፖሊሲው በ2030 ዓ.ም በገጠር መዋቅራዊ ለውጥ በማምጣት ዘርፉን ለማሻገር እና ሀገራዊ ብልጽግናን ማረጋገጥ እንደሚያስችል ተናግረዋል።

በዋናነትም ስንዴ እና ሩዝን ጨምሮ በመንግስት የተቀመጡ አስር ስትራቴጂክ ምርቶችን በፍጥነት ለማሳደግ ሰፊ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም