በዘንድሮ የበጋ መስኖ ስንዴ እስካሁን ከ1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በዘር ተሸፍኗል - ኢዜአ አማርኛ
በዘንድሮ የበጋ መስኖ ስንዴ እስካሁን ከ1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በዘር ተሸፍኗል
አዲስ አበባ፤ ህዳር 25/2017(ኢዜአ):- በዘንድሮ የበጋ መስኖ ስንዴ እስካሁን ከ1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በዘር መሸፈኑን ግብርና ሚኒስቴር ገለጸ።
በበጋ የመስኖ ስንዴ ልማትም 173 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዶ በሁሉም ክልሎች ወደ ስራ መገባቱን አስታውቋል።
በግብርና ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ ከበደ ላቀው ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በግብርና ልማት ምርትና ምርታማነትን የማሳደግ ስራ በተጠናከረ መልኩ ቀጥሏል ብለዋል።
በተለይም በለውጡ አምስት አመታት ለበጋ መስኖ ስንዴ የተሰጠው ትኩረት ትልቅ ሀገራዊ አቅም መሆኑን አንስተዋል።
በስንዴ ልማት ከሀገር ውስጥ ፍጆታ በማለፍም ለውጭ ገበያ በማቅረብ የተሳካ ውጤት የተገኘ መሆኑን ገልጸዋል።
ዘንድሮ የደረሱ የመኸር ሰብሎችን ከመሰብሰብ ጎን ለጎን የበጋ መስኖ ስንዴ የዝግጅት ምዕራፍ ተጠናቆ ወደ ተግባር መገባቱንም ተናግረዋል።
በዘንድሮ የበጋ መስኖ ስንዴ 4 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በማረስ 173 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት መታቀዱን ገልጸዋል።
በእስካሁኑ ሂደትም 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ታርሶ ከዚህም ከ1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሄክታሩ በዘር ተሸፍኗል ብለዋል።
ከበጋ መስኖ ስንዴ ጎን ለጎን የመደበኛ መስኖ፤ የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት በልዩ ትኩረት እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
የግብርና መካናይዜሽን እና ግብዓቶችን የማቅረብ ሥራም በተጠናከረ መልኩ ቀጥሏል ብለዋል።