ቀጥታ፡

የፋርማሲ ባለሙያዎች ህገወጥ የመድኃኒት ዝውውርን ለመከላከልና አግባብነት ያለው የፀረ ተህዋስያን መድኃኒት አወሳሰድ እንዲኖር ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል

የፋርማሲ ባለሙያዎች ህገወጥ የመድኃኒት ዝውውርን ለመከላከልና አግባብነት ያለው የፀረ ተህዋስያን መድኃኒት አወሳሰድ እንዲኖር ለማድረግ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ተጠየቀ። 

የኢትዮጵያ ፋርማሲ ማህበር የተመሰረተበትን 50ኛ አመት የወርቅ ኢዮቤልዩ በዓል አስመልክቶ ለሁለት ቀናት የሚቆይ ጉባኤ እያካሄደ ይገኛል።


 

በዚህ ወቅት የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጄ ድጉማ እንዳሉት መንግስት የአገር ውስጥ አምራቾችን አቅም በማጠናከር የአገር ውስጥ የህክምናና መድኃኒት ምርትን ለማሻሻል የሚያስችሉ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል። 

በጤናው ዘርፍ  የመንግስትና የግል ዘርፉን አጋርነት ለማጠናከር በተለይ ከግል መድኃኒት አምራቾች ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል። 

የፋርማሲ አገልግሎቱን ዘመናዊ ለማድረግ የሚያስችሉ የህግ ማሻሻያዎችና የመረጃ ስርዓቶችን የማበልጸግና መሰል ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም ጠቅሰዋል። 

ማህበሩ ባለፉት 50 አመታት በጤናው ዘርፍ አስተዋጽኦ ሲያበረክት መቆየቱን በበጎ አንስተው የአባላቱን አቅም ለማጎልበት እያከናወነ ያለው ተግባር የሚበረታታና ለሌሎች ማህበራት ተሞክሮ ይሆናል ብለዋል።

በአለም አቀፍ ደረጃ ተግዳሮት እየሆነ የመጣውን የፀረ ተህዋስያን መድኃኒት መላመድ ችግርን ለመፍታት አግባብነት ያለው የፀረ ተህዋስያን አጠቃቀም እንዲኖር የማህበሩ አባላት የበኩላቸውን መወጣት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል። 

ደረጃቸውን ያልጠበቁና ማረጋገጫ የሌላቸው መድኃኒቶችና ህገወጥ የመድኃኒት ዝውውር  የጤና አገልግሎቱን ችግር ውስጥ የሚከቱ በመሆናቸው ይህን ለመቆጣጠር በሚደረገው ጥረት ማህበሩ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል። 

ማህበሩ የፋርማሲ ባለሙያዎች ሙያዊ ስነምግባርን ተከትለው ስራቸውን እንዲያከናውኑ ለማስቻል የጀመረውን ስራ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል። 

የማህበሩ ፕሬዝዳንት ዶክተር ዳንኤል ዋቅቶሌ በበኩላቸው ማህበሩ ባለፉት 50 አመታት ጤናው የበለፀገ ማህበረሰብ ለመፍጠር ሲሰራ መቆየቱንና በቀጣይም ይህን ተግባር አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል ። 

ኢትዮጵያ ከ60 አመት ጀምሮ መድኃኒት በዘመናዊ መልኩ እያመረተች ብትሆንም በጀመረችበት ፍጥነት መቀጠል አለመቻሏን ጠቅሰዋል። 

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በዘርፉ የነበረውን የውጭ ምንዛሬ እጥረት ለመፍታት ያስቻለ መሆኑን ጠቁመው አሁን ላይ አምራቾች በሙሉ አቅማቸው እንዲያመርቱ ለማስቻል የስራ ማስኬጃ የፋይናንስ አቅርቦት በበቂ መጠን እንዲቀርብም ጠይቀዋል። 

የህገወጥ መድኃኒት ዝውውርን መከላከል የሁሉንም ጥረት የሚጠይቅ መሆኑንና ማህበሩም በዚህ ረገድ በትብብር ለመስራት ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል። 

ማህበሩ ላሉት 4ሺህ ያህል አባላት በሚሰጠው የሙያ ማጎልበቻ ስልጠና ስነምግባርን ማዕከል አድርጎ እየሰራ መሆኑንና የመድኃኒት አጠቃቀም ላይ በጋራ እየሰራ ነው ብለዋል። 

ማህበሩ ያለፈውን ማክበር፣ የአሁኑን ማስተካከልና የወደፊቱን መተለም በሚል መሪ ሃሳብ ለማህበሩ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት እውቅና ሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም