ቀጥታ፡

የገጠር ኢንዱስትሪን ማስፋፋት በግብርናው ዘርፍ እየመጣ ያለውን ተጨባጭ ዕድገት ለማስቀጠል ከፍተኛ ሚና ይጫወታል - አቶ መላኩ አለበል

አዲስ አበባ፤ህዳር 25/2017 (ኢዜአ) ፡-የገጠር ኢንዱስትሪን ማስፋፋት በግብርናው ዘርፍ እየመጣ ያለውን ተጨባጭ ዕድገት ለማስቀጠል ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ገለጹ።

የኢንዱስትሪ ሚኒሰቴር የ2017 ዓ.ም የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄን አስመልክቶ በሸገር ከተማ አስተዳደር ከሚገኙ የመንግስት አመራሮችና የአምራች ኢንዱስትሪ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሄዷል።

የውይይቱ ዓላማ የከተማ አስተዳደሩን የአምራች ኢንዱስትሪ እንቅስቃሴ ለማበረታታትና በዘርፉ የሚሰማሩ ኢንቨስተሮች በአሰራር ሂደት የሚገጥሟቸውን ችግሮች መፍታት ላይ ያተኮረ መሆኑ ተገልጿል።


 

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል እንደ ሀገር በኢንዱስትሪው ዘርፍ ለመበልጸግ ከከተሞች እኩል ለገጠር ኢንዱስትሪ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ ገልጸዋል።

ግብርናና ኢንዱስትሪ በተፈጥሯቸው ተመጋጋቢ እንደ መሆናቸው መጠን የገጠር ኢንዱስትሪን ማስፋፋት በግብርናው ዘርፍ እየመጣ ያለውን ተጨባጭ እድገት ለማስቀጠል ከፍተኛ ሚና ይጫወታል ሲሉ ተናግረዋል።

የከተማ አስተዳደሩ አመራሮችም በበኩላቸው ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አምራች ኢንዱስትሪዎችን ለመደገፍና ለማበረታታት ለሚያደርገው ጥረት ምስጋና አቅርበዋል።

ሚኒስትሩ ከተማ አስተዳደሩ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ዓላማን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ለአምራች ኢንዱስትሪው ትኩረት እንዲሰጡና በዘርፉ የሚሰማሩ ባለሀብቶችን በቅርበት እንዲደግፍ አቅጣጫ መስጠታቸውን ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም