በኢንዱስትሪ ፓርኩ ቡና፣ ማርና አቮካዶ ምርቶችን በማቀነባበር እሴት ጨምረው ለገበያ የሚያቀርቡ ሶስት ባለሀብቶች ስራ ሊጀምሩ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በኢንዱስትሪ ፓርኩ ቡና፣ ማርና አቮካዶ ምርቶችን በማቀነባበር እሴት ጨምረው ለገበያ የሚያቀርቡ ሶስት ባለሀብቶች ስራ ሊጀምሩ ነው

ሀዋሳ ህዳር 25/2017 (ኢዜአ) :- በይርጋለም የተቀናጀ የግብርና ኢንዱስትሪ ፓርክ ቡና፣ ማርና አቮካዶ ምርቶችን በማቀነባበር እሴት ጨምረው ለገበያ የሚያቀርቡ ሶስት ባለሀብቶች በተያዘው አመት ስራ እንደሚጀምሩ የሲዳማ ክልል ኢንደስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን አስታወቀ ።
የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሀይሉ የተራ ለኢዜአ እንደገለጹት በፓርኩ 29 የሚደርሱ ባለሃብቶች የተለያዩ የግብርና ምርቶች ለማቀነባበር የሚያስችላቸውን ውል ፈጽመው በተለያየ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።
በተያዘው ዓመትም ቡና፣ ማርና አቮካዶ ምርቶችን በማቀነባበር እሴት ጨምረው ለገበያ የሚያቀርቡ ሶስት አዳዲስ ባለሃብቶች ስራ እንደሚጀምሩ ገልጸዋል።
በፓርኩ 36 ነጥብ 5 ከመቶ የሚሆን የለማ መሬትና ሼድ ለባለሃብቶች የተላለፈ ሲሆን ቀሪውም ቦታ ለባለሃብቶች መዘጋጀቱን ተናግረዋል።
በፓርኩ ለማልማት የሚፈልጉ ባለሃብቶች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን የገለጹት ዋና ስራ አስፈጻሚው የተለያዩ መድረኮችን በማዘጋጀት ፓርኩን የማስተዋወቅ ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።
በፓርኩ እያመረቱ የሚገኙ ባለሃቶች ብቻ ከ24 ሺህ ለሚበልጡ ዜጎች የስራ እድል መፍጠራቸውን ገልጸው ከቅጥር በተጨማሪ በማህበር ተደራጅተው ግብዓት የሚያቀርቡ ወጣቶች እንደሚገኙበትም ገልጸዋል።
ባለፉት አራት ዓመታትም 42 ሺህ ቶን የሚጠጋ የአቮካዶ፣ ወተትና ማር ምርቶችን ላይ እሴት ጨምሮ ለውጭ ገበያ በማቅረብ 15 ነጥብ 6 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ማግኘት ተችሏል ብለዋል።
ከውጭ የሚገቡ የወተትና ጁስ ምርቶችን በሃገር ውስጥ በመተካት 13 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ገቢ መገኘቱን ገልጸዋል።
የይርጋለም የተቀናጀ የግብርና ኢንደስትሪ ፓርክ በሃገሪቱ ካሉ አራት የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ፓርኮች አንዱ ሲሆን በ2013 መጋቢት ወር ላይ ነው ስራ የጀመረው።