ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያን ብሔራዊ ኩራትና የአፍሪካውያን የብልፅግና ተምሳሌት ነው- አፈ-ጉባዔ ታገሰ ጫፎ - ኢዜአ አማርኛ
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያን ብሔራዊ ኩራትና የአፍሪካውያን የብልፅግና ተምሳሌት ነው- አፈ-ጉባዔ ታገሰ ጫፎ
አዲስ አበባ፤ህዳር 25/2017(ኢዜአ)፦ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያን ብሔራዊ ኩራትና የአፍሪካውያን የብልፅግና ተምሳሌት መሆኑን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ታገሰ ጫፎ ገለጹ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነ የፓርላማ የዜጎች ፎረም ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በተገኙበት አካሂዷል።
የምክር ቤቱ አፈ-ጉባዔ ታገሰ ጫፎ በመክፈቻ ንግግራቸው የፓርላማ የዜጎች ፎረም የሀሳብ ማንሸራሸሪያ መድረክ መሆኑን አንስተዋል።
ፎረሙ በአሁናዊ፣ የዓለም ፖለቲካና ዲፕሎማሲ፣ የመሪዎች ሚና እና የሕዝብ ተሳትፎ እንዲሁም ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ከፓን-አፍሪካዊነት እሳቤ አኳያ ምክክር እንደሚደረግበት ገልፀዋል።
ለሀገርና ለሕዝብ ተጠቃሚነት የላቀ ሚና ያላቸውና የፖሊሲ ግብዓት የሚሆኑ ሀሳቦች የሚሰባሰቡበት፣ የጋራ ግንዛቤ የሚፈጠርበትና ለትግበራውም በትብብር በመቆም የምንተጋበት ነው ብለዋል።
በአፍሪካ ትልቁ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከምህንድስና በላይ የሆነ የአህጉሪቷ የጋራ የዕድገትና ብልጽግና መሠረት መሆኑን አፈ-ጉባዔ ታገሰ አንስተዋል።
ግድቡ የኢትዮጵያውያን የብርሃንና የልዕልና መገለጫ ነው ያሉት አፈ-ጉባዔው፤ አፍሪካውያን የተፈጥሮ ኃብታቸውን ለዘላቂ ልማት ማዋልና ከትሩፋቱ መቋደስ እንደሚገባቸው ተናግረዋል።
አፈ-ጉባዔው አክለውም ኢትዮጵያም የሁሉንም የተፋሰሱ አገራት ተጠቃሚነት ታሳቢ ባደረገ መልኩ ለጋራ እድገት እየሰራች መሆኑን ተናግረዋል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ ቤልጅጌ (ዶ/ር) በፎረሙ ላይ ሕዳሴ ግድብን ከፓን-አፍሪካኒዝም አኳያ የቃኘ ጽሑፍ አቅርበዋል።
እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ ግድቡ የኃይል ማመንጫ ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ የብሔራዊ ኩራት ለአፍሪካውያን ደግሞ አስተሳሳሪ የፓን-አፍሪካ ፕሮጀክት ነው።
በኢትዮጵያውያን ዕውቀት፣ ኃብት፣ ደምና ላብ የተገነባ መሆኑን ጠቅሰው፤ ግድቡ ከሀገር ባለፈ ለቀጣናዊ ኢኮኖሚ ትስስርና አንድነቷ ለተጠናከረ አፍሪካ እውን መሆን ግዙፍ ፋይዳ አለው ብለዋል።
የፓን-አፍሪካኒዝም እሳቤ የበለፀገችና የተረጋጋች አፍሪካ መገንባት እንደሆነ ገልጸው፤ ኢትዮጵያ ደግሞ ከአፍሪካውያን ነጻነት እስከ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፋና ወጊ ሥራ ሰርታለች ነው ያሉት።
በመሆኑም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብም የአጀንዳ 2063 ዕውን እንዲሆን እና የዘመኑ የፓን- አፍሪካኒዝም እሳቤ እንዲሳካ የሚያደርግ በመሆኑ ኢትዮጵያውያን ሚናችንን አጉልተን ማስተዋወቅ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁርና የሃይድሮ ፖለቲካ ተመራማሪው ያዕቆብ አርሳኖ (ዶ/ር)፤ ኢትዮጵያ የውሃ ሀብቷን እንዳትጠቀም የነበሩ አግላይ ስምምነቶችን እና የታላቁ ኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዕውን እንዳይሆን የነበረውን ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ጫና አንስተዋል።
ኢትዮጵያ በመንግሥት ቁርጠኝነት፣ በህዝብ ተሳትፎና ሀገራዊ አርበኝነት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታን በማሳካትና የዲፕሎማሲ ፈተናዎችን በመቀልበስ ድል መቀዳጀቷንም አብራርተዋል።
የግድቡ መገንባት ለአካባቢው አገራት የኤሌክትሪክ ኃይል ትስስር ትልቅ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ በውኃ ኃብቷና እንደ ሕዳሴ ግድብ ባሉ ግዙፍ የመሠረተ-ልማት አውታሮቿ ለባህር ረገጥ ሀገራት እያበረከተች ካለው ሚና አንጻር የባህር በር ጥያቄዋ ምላሽ ሊያገኝ እንደሚገባም ጠቁመዋል።
ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት ንጹስ ኮሚቴ ሰብሳቢ አምባሳደር (ዶ/ር) ቶውፊቅ አብዱላሂ፤ የታላቁ ኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ በራስ አቅም ተጀምሮ በለውጡ መንግስት ቆራጥ ውሳኔ ወደ ማጠናቀቂያ ምዕራፍ መድረሱ ሀገራዊና ቀጣናዊ ሚናችንን የሚያሳድግ ነው ብለዋል።
በግድቡ ጉዳይ የነበሩ ድርድሮች በአፍሪካ ህብረት ማዕቀፍ ስር እንዲካሄዱ መደረጉም ኢትዮጵያ አፍሪካዊ ችግሮችን በአፍሪካ መፍታት የሚለውን መርሆዋን ያጸና መሆኑን ተናግረዋል።
ግድቡን ለማሰናከል ያልተደረገ ሙከራ እንዳልነበር አስታውሰው፤ ግድቡ የከፍታችን ዘመን ማብሰሪያ ምልክት ወደ መሆን ተሸጋግሯል ብለዋል።