ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የመንግሥት ቁርጠኝነት፣ የህዝብ ተሳትፎ እና የጠንካራ ዲፕሎማሲ ጥረት ውጤት ነው- ፕሮፌሰር ያዕቆብ አርሳኖ - ኢዜአ አማርኛ
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የመንግሥት ቁርጠኝነት፣ የህዝብ ተሳትፎ እና የጠንካራ ዲፕሎማሲ ጥረት ውጤት ነው- ፕሮፌሰር ያዕቆብ አርሳኖ
አዲስ አበባ፤ህዳር 25/2017(ኢዜአ)፦የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የመንግሥት ቁርጠኝነት፣ የህዝብ ተሳትፎ እና የጠንካራ ዲፕሎማሲ ጥረት ውጤት መሆኑን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ምሁሩና የግድቡ ተደራዳሪ ፕሮፌሰር ያዕቆብ አርሳኖ ገለጹ።
በተለያዩ ሀገራዊ እና አህጉራዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ የመጀመሪያው የፓርላማ የዜጎች ፎረም ተካሂዷል።
በመድረኩም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ምሁሩና የህዳሴ ግድብ ተደራዳሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ያዕቆብ አርሳኖ፤ በውሃ ዲፕሎማሲ የነበሩ ታሪኮች፣ተጋድሎና ፈተናዎችን የተመለከተ ፅሁፍ አቅርበዋል።
ኢትዮጵያ የውሃ ሀብቷን እንዳትጠቀም የነበሩ አግላይ ስምምነቶችን እና የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ዕውን እንዳይሆን የነበረውን ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ጫናም አንስተዋል።
ኢትዮጵያም የነበሩ ፈተናዎችን በመቋቋም የሕዳሴ ግድብ ግንባታን ዕውን ያደረገችበትን ሁኔታ በስፋት አንስተዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ እውን መሆን የመንግሥት ቁርጠኝነት፣ የህዝብ ተሳትፎ እና የጠንካራ ዲፕሎማሲ ጥረት ውጤት መሆኑን ነው ያብራሩት።
የግድቡ መገንባት ከኢትዮጵያም ባለፈ ለአካባቢው አገራት የኤሌክትሪክ ኃይል ትስስር ትልቅ እድል የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘት ጥረትም ከአባይ ፖለቲካ ያልተናነሰ ትልቅ ጉዳይ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በአጠቃላይ በውሃ ዲፕሎማሲ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ ዩኒቨርሲቲዎችን ጨምሮ ሁሉም ባለድርሻ ተቋማት የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ ይገባል ብለዋል።