ቀጥታ፡

በአማራ ክልል ለዘንድሮው የበጋ ወቅት የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃና ልማት ስራ ዝግጅት እየተደረገ ነው 

ባህር ዳር ፤ ህዳር 25/2017 (ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል በዘንድሮው የበጋ ወራት ለሚከናወነው የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃና ልማት ስራ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

ከዝግጅቱ መካከል ለ280 ሺህ 700 ቀያሽ አርሶ አደሮች ስልጠና መስጠት መጀመሩ ተጠቅሷል።

የክልሉ ግብርና ቢሮ  የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ አጠቃቀም ዳይሬክተር አቶ እስለዓለም ምህረት ለኢዜአ እንዳመለከቱት፤ ባለፉት ዓመታት በክልሉ የተከናወነው የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራ የአካባቢው ስነ-ምህዳር ወደነበረበት እየተመለሰ እንዲመጣ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል።

ይህም የአፈር ክለት እንዲቀንስና ለምነቱ እየጨመረ እንዲመጣ ከማድረግ ባለፈ ተፋሰሶቹ በቂ የእንስሳት መኖ መገኛ ምንጭ እየሆኑ መምጣታቸውን ተናግረዋል።

ስራውን አጠናክሮ ለማስቀጠል በዘንድሮው የበጋ ወራት የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራው  በዘጠኝ ሺህ 67 ተፋሰሶች እንደሚከናወን ገልጸዋል።


 

ይህም መላ ህብረተሰቡን በማሳተፍ በመጪው ታህሳስ ወር መጨረሻ ለሚጀመረው የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራ አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።

የልማት ስራውም በተራቆተ 366 ሺህ 300 ሄክታር መሬት ላይ የማሳና የጋራ ላይ ዕርከን፣ እንዲሁም የተለያዩ የውሃ ማስረጊያ " ስትራክቸሮች " ይከናወናሉ ብለዋል።

በሁሉም የክልሉ ዞኖችና ቀበሌዎች በሚከናወነው የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራ ከ4 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ ህዝብ በልማት ስራው እንደሚሳተፉ የሚጠበቅ መሆኑን አመልክተዋል።

ለዚህም ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ከሰብል ምርት ስብሰባው ጎን ለጎን የተጀመረው የቀያሽ አርሶ አደሮች ስልጠና እስከ ቀጣዩ ወር አጋማሽ ተጠናቆ ወደ ተግባር ስራ እንደሚገባ አብራርተዋል።

ለልማት ስራው ከሚያስፈልገው እስካሁን ከ2 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ  አካፋ፣ ዲጅኖና ሌሎች የስራ መሳሪያዎች መለየታቸውን ዳይሬክተሩ ጠቅሰዋል።

በምዕራብ ጎጃም ዞን የሰከላ ወረዳ አርሶ አደር አላምረው ሞላ በሰጡት አስተያየት፤ ባለፉት ዓመታት ያከናወኑት የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራ ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው ተናግረዋል።


 

በእርሻ ማሳቸው ላይ የተከናወነው የዕርከን ስራ የአፈር ክለትና መሸርሸር እየቀነሰ እንዲመጣ ከማድረግ ባለፈ የምርት ጭማሪ እንዲያገኙ ማስቻሉን ገልጸዋል።   

በያዝነው የበጋ ወቅት በሚካሄደው የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራ ያለማንም ቀስቃሽ ግንባር ቀደም ሆነው በስራው ለመሳተፍ  እንደተዘጋጁም ተናግረዋል።

ባለፉት ዓመታት ባከናወነው የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራ ተጠቃሚ ሆነናል'' ያሉት ደግሞ በደቡብ ጎንደር ዞን የፋርጣ ወረዳ አርሶ አደር መንጌ መንግስቴ ናቸው።

የመሬቱ ለምነት በየጊዜው አየተሻሻለ መምጣቱ ምርታማነት እንዲጨምርና ከተፋሰሶች በቂ የእንስሳት መኖ እንዲያገኙ እያስቻላቸው መሆኑን ገልጸዋል።

በያዝነው ዓመትም ስራውን በእኔነት ስሜት ለማከናወን ተግባሩ የሚጀመርበትን ቀን እየተጠባበቁ እንደሚገኙ አስታውቀዋል።

በአማራ ክልል ባለፉት ዓመታት የተከናወነው የበጋ ወራት የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራ  በውጤታማ መሆኑን ከግብርና ቢሮው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም