ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኃይል ማመንጫ ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ኩራት፤ ለአፍሪካውያን ደግሞ የፓን-አፍሪካ ፕሮጀክት ነው - ኢዜአ አማርኛ
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኃይል ማመንጫ ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ኩራት፤ ለአፍሪካውያን ደግሞ የፓን-አፍሪካ ፕሮጀክት ነው
አዲስ አበባ፤ህዳር 25/2017(ኢዜአ)፦ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኃይል ማመንጫ ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ኩራት፤ ለአፍሪካውያን ደግሞ የፓን-አፍሪካ ፕሮጀክት ነው ሲሉ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትሩ ተስፋዬ ቤልጅጌ (ዶ/ር) ገለጹ።
ተስፋዬ ቤልጅጌ (ዶ/ር) በፓርላማ የዜጎች ፎረም ላይ ሕዳሴ ግድብን ከፓን-አፍሪካኒዝም አኳያ የቃኘ ጽሑፍ አቅርበዋል።
በገለጻቸውም፤ግድቡ የኃይል ማመንጫ ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ የብሔራዊ ኩራት፤ለአፍሪካውያን ደግሞ የፓን-አፍሪካ ፕሮጀክት ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያውያን ዕውቀት፣ ኃብት፣ ላብና ጉልበት የተገነባ ቢሆንም ለቀጣናዊ ኢኮኖሚ ትስስር ካለው ፋይዳ አኳያ የፓን-አፍሪካኒዝም ፕሮጀክት እንደሚያደርገው ገልፀዋል።
አፍሪካውያን ፕሮጀክት ቀርፀው፣ በራሳቸው ኃብት አሰባስበው የራሳቸውን ተፈጥሮ ኃብቶች መጠቀም እንደሚችሉ አስተሳሰብ የለወጠ መሆኑን ተናግረዋል።
የፓን-አፍሪካኒዝም እሳቤ መነሻው የጥቁር ሕዝብ የእኩልነትና የፍትህ ንቅናቄ መነሻ እንደሆነ ገልፀው፤ በ21ኛው ክፍለ ዘመንም አፍሪካውያንን ያሰባሰበው እሳቤ ነው ብለዋል።
ፖን-አፍሪካኒዝም እሳቤ የበለፀገና የተረጋጋ አፍሪካ መገንባት ከሆነ ኢትዮጵያ ደግሞ ለዚህ ፋናወጊ ሀገር መሆኗን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በታሪክ ለአፍሪካ ነፃነት የሞራል ስንቅ እንዲሁም ተግባር ተኮር አበርክቶ የነበራት እንዲሁም የተፃረሩ ኃሳቦችን አስታርቃ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እንዲፈጠር ያደረገች አገር መሆኗን አንስተዋል።
በዚህም ኢትዮጵያ ትናንት ብቻ ሳይሆን ዛሬም ሕዳሴ ግድብን በመገንባት የፓን-አፍሪካኒዝም ቀዳሚ ተሰላፊ መሆኗን አንስተዋል።
ይህም የአጀንዳ 2063 ዕውን እንዲሆን ያግዛልም ነው ያሉት። ግድቡ የዘመኑ ፓን-አፍሪካኒዝም መጠናከር አንዱ ማሳያ እንደሆነም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያውያን አሁንም በብሔራዊ ጥቅም ጉዳይ የተቀራረበ አቋም መያዝ ይገባናል ብለዋል።
ለዚህ ደግሞ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለሀገራዊ መግባባትና አንድነት መሥራት ይጠይቃልም ብለዋል።
ኢትዮጵያ ለጎረቤቶቿና ለአፍሪካ የከፈለችው ዋጋ፣ እሳቤዋና ተጨባጭ ተግባሯን ለአፍሪካውያን መሸጥ ይገባልም ነው ያሉት።
ለዚህ ደግሞ ምሁራን፣ ሚዲያና የኪነ-ጥበብ ሰዎች ቁልፍ ሚና እንዲወጡ ጠይቀዋል።
ኢትዮጵያ ለፓን-አፍሪካኒዝም ያላትን የመሪነት ሚና ለማስቀጠል የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት ማረጋገጥና ውስጣዊ አንድነትን ማጠናከር እንደሚገባ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄም በዚሁ ማዕቀፍ የሚታይ ቁልፍ አጀንዳ መሆኑንም እንዲሁ።