ቀጥታ፡

19ኛው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በክልል ደረጃ የማጠቃለያ በዓል በጎንደር ከተማ እየተከበረ ነው

አዲስ አበባ፤ህዳር 25/2017(ኢዜአ)፦"አገራዊ መግባባት ለሕብረ-ብሔራዊ አንድነት" በሚል መሪ ኃሳብ የሚከበረው 19ኛው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በክልል ደረጃ የማጠቃለያ በዓል በጎንደር ከተማ እየተከበረ ነው።

በመርኃ-ግብሩ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር፣ የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ/ር)፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ፋንቱ ተስፋዬን ጨምሮ የሌሎች ክልሎች የምክር ቤት አፈ-ገባኤዎችና ሌሎች የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል። 

የጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው በዚህ ጊዜ እንደገለጹት፤ የጎንደር ከተማ በለውጥ ሂደት ላይ ነች።

19ኛው የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓልን ለመታደም የተገኙ እንግዶችም የተሰሩ ፕሮጀክቶችን በመጎብኘት ማረጋገጥ እንደሚችሉ ገልፀዋል።

የጎንደር ከተማ 20ኛውን የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን የማክበር ፍላጎት እንዳላት ጠቁመዋል።  


 

የጎንደር ከተማ 20ኛውን የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል ማክበር የሚያስችል አቅም እንዳላት ገልጸው፤ ይሄንን ታሳቢ ያደረገ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል።

የጎንደር ከተማ ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ እናትነሽ ዋለ የዘንድሮው የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል የአማራ ክልል ማጠቃለያ መርኃ-ግብር በጎንደር መከበሩ ልዩ ትርጉም አለው ብለዋል።

በዓሉ በጎንደር ከተማ ሲከበር የከተማዋ የልማትና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ እያገኙ ባሉበት ወቅት መሆኑን ገልፀዋል።

የአፄ ፋሲል ግንብ እድሳት፣ የአዘዞ-ቡልኮ መንገድና የመገጭ ፕሮጀክቶች የዚህ ማሳያዎች መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአማራ ለተጀመሩ የልማት ሥራዎች ለሰጡት ድጋፍና ክትትል ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም