ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ለኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን አጀንዳቸውን አስረከቡ

አዲስ አበባ፤ህዳር 25/2017 (ኢዜአ) ፡-የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ለኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን አጀንዳቸውን ዛሬ አስረክበዋል።

አጀንዳዎቹን ለኮሚሽኑ የስራ ኃላፊዎች ያስረከቡት የጋራ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን አየለ እና የስራ አስፈጻሚ አባላት ናቸው።

የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ያስረከቡት አጀንዳም ከሁሉም ፓርቲዎች የተሰበሰቡና ወሳኝ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ መሆናቸው ተገልጿል።

በኢትዮጵያ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት ሚናቸውን ሲወጡ መቆየታቸውም በዚሁ ወቅት ተጠቁሟል።

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲ የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን አየለ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ምክር ቤቱ ለሀገራዊ ምክክሩ ዕውን መሆን የበኩሉን እየተወጣ ይገኛል።

ምክር ቤቱ ለኢትዮጵያ ልማት ፣ሰላምና ዴሞክራሲ መረጋገጥ የበኩሉን ይወጣል ብለዋል።

አጀንጃዎቹም ከሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች የተሰበሰቡና በጠቅላላ ጉባኤም የጸደቁ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

አጀንዳዎቹ በሰባት ዋና ዋና ክፍሎች እና በ64 ዝርዝር ጉዳዮች የተጠናከሩ መሆናቸውን አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ኮሚሽኑ ከታህሳስ 5 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ በኦሮሚያ ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብ ስራውን ይጀምራል ብለዋል።

በዚህም ለዋናው የምክክር ሂደት ተሳታፊ የሚሆኑ ባለድርሻ አካላት እንደሚመረጡ ገልጸዋል።

በትግራይ እና በአማራ ክልሎች ሂደቱን የማከናወን ስራ ለመጀመር እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም