ቀጥታ፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የአፍሪካ የጋራ ቅርስ እና የአፍሪካ የብልፅግና ተምሳሌት ነው- አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ

አዲስ አበባ፤ህዳር 25/2017 (ኢዜአ) ፡-የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የአፍሪካ የጋራ ቅርስ እና የአፍሪካ የብልፅግና ተምሳሌት መሆኑን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ ገለጹ።

አፈ ጉባዔው በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአይነቱ የመጀመሪያ የሆነውን የፓርላማ የዜጎች ፎረም በይፋ ከፍተዋል።

አፈ ጉባዔው በፎረሙ መክፈቻ ላይ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር የፓርላማ የዜጎች ፎረም የሀሳብ ማንሸራሸሪያ መድረክ ነው ብለዋል።

ፎረሙ በአሁናዊ የዓለም ፖለቲካና ዲፕሎማሲ፣ የመሪዎች ሚና እና የህዝብ ተሳትፎ እንዲሁም ሕዳሴ ግድብን ከፓን አፍካዊነት እሳቤ እንደሚቃኝ ገልጸዋል።


 

በፎረሙ ለሀገርና ለህዝብ ተጠቃሚነት የላቀ ሚና ያላቸው የፖሊሲ ግብዓት ሀሳቦች የሚሰባሰቡበት፣ የጋራ ግንዛቤ መፍጠርና ለትግበራውም በትብብር መቆም የምንተጋበት ነው ብለዋል።

የታላቁ የሕዳሴ ግድብ በአፍሪካ ትልቁ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ብቻ ሳይሆን የጋራ ዕድገትና ትብብር መሰረት እንደሆነ ገልጸዋል።

ግድቡ የአፍሪካ የጋራ ቅርስ እና የአፍሪካ የብልፅግና ተምሳሌት መሆኑንም አመልክተዋል።

አፍሪካዊያን የተፈጥሮ ሀብታቸውን ለዘላቂ ልማት ማዋልና ከትሩፋቱ መቋደስ እንደሚችሉ ያሳየ ነው ያሉት አፈ ጉባዔው፥ ግድቡ ለምስራቅ አፍሪካ ቀጣናዊ አቅም እንደሆነም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያም በዲፕሎማሲው መስክ ሁሉንም የተፋሰሱ ሀገራት የጋራ ተጠቃሚና አሸናፊ በሚያደርግ ዲፕሎማሲ እንደምታምን ገልጸዋል።

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም