ቀጥታ፡

የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል ምክንያት በማድረግ ሩጫ በአርባምንጭ እየተካሄደ ነው

አርባምንጭ ፤ ህዳር 25/2017(ኢዜአ)፦ 19ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓልን ምክንያት በማድረግ ሩጫ በአርባምንጭ ከተማ እየተካሄደ ነው።

ሩጫው "አሻራችን ለስታዲዮማችን" በሚል መሪ ሃሳብ መነሻና መድረሻ ጋሞ አደባባይ የሆነ አምስት ኪሎ ሜትር የሚሸፍን  ነው። 

በመረሃ ግብሩ ላይ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ እንደተናገሩት ፤ የሩጫው ዓላማ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ምክንያት በማድረግ ሲሆን ሌላው ደግሞ  የአርባምንጭ ስታዲዮም የግንባታ ሂደትን በገቢ ለመደገፍ ነው።


 

አቶ ጥላሁን በአርባምንጭ ከተማ  እየተገነባ ያለውን ስታዲዮም ከማጠናቀቅም በላይ ሌሎች ልማቶችን በማከናወን የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ አበክረን እንሰራለን ብለዋል።

ለዚሁ መርሃ ግብር የተዘጋጁ ቲ-ሸርቶች ሽያጭ ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ ሲካሄድ የቆየ ሲሆን፤  ሁሉም የሩጫው ተሳታፊዎች በዚሁ ደምቀው በመሮጥ ላይ ይገኛሉ።

በመርሃ ግብሩ በየደረጃው የሚገኙ የመንግስት የሥራ ሃላፊዎች ፤ አትሌት ሙክታር እድሪስና ሌሎችም ታዋቂ አትሌቶች እንዲሁም የክልሉ የህብረተሰብ ክፍሎች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ። 

19ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል "ሀገራዊ መግባባት ለህብረ ብሔራዊ አንድነት" በሚል መሪ ሀሳብ  በአርባምንጭ ከተማ ህዳር 29/2017 ዓ.ም ይከበራል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም