ታሪካዊ ተቀናቃኞቹ አርሰናል እና ማንችስተር ዩናይትድ የሚያደርጉት የሊጉ ጨዋታ ተጠባቂ ነው 

አዲስ አበባ፤ ህዳር 25/2017(ኢዜአ):- በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የ14ኛ ሳምንት መርሃ ግብር አርሰናል ከማንችስተር ዩናይትድ የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል።

የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ከምሽቱ 5 ሰዓት ከ15 በኤምሬትስ ስታዲየም ይደረጋል።

አርሰናል በሊጉ ባደረጋቸው 13 ጨዋታዎች 7 ጊዜ ሲያሸንፍ 2 ጊዜ ተሸንፏል። 4 ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥቷል።

መድፈኞቹ በጨዋታዎቹ 26 ጎሎችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፉ 14 ግቦችን አስተናግደዋል። 

በ42 ዓመቱ ስፔናዊ አሰልጣኝ ማይክል አርቴታ የሚመራው አርሰናል በ25 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ተጋጣሚው ማንችስተር ዩናይትድ በውድድር ዓመቱ ባደረጋቸው 13 ጨዋታዎች 5 ጊዜ ሲያሸንፍ 4 ጊዜ ተሸንፏል። በቀሪዎቹ 4 ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርቷል።

ቀያዮቹ ሴጣኖች 17 ጎሎችን ሲያስቆጥሩ 13 ግቦችን አስተናግደዋል። 

በ39 ዓመቱ ፖርቹጋላዊ ሩበን አሞሪም የሚሰለጥነው ማንችስተር ዩናይትድ በ19 ነጥብ 9ኛ ደረጃን ይዟል።

ሁለቱ ክለቦች በሁሉም ውድድሮች ሲገናኙ የአሁኑ ለ241ኛ ጊዜ ነው። ከዚህ ቀደም በነበራቸው 241 የእርስ በእርስ ግንኙነቶች ማንችስተር ዩናይትድ 99 ጊዜ አሸንፏል።

አርሰናል 89 ጊዜ ሲያሸንፍ 53 ጊዜ አቻ ወጥተዋል።

አርሰናል እና ማንችስተር ዩናይትድ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ታሪካዊ ተቃናቃኞች የሚባሉ ቡድኖች ናቸው።

ክለቦቹ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኙት እ.አ.አ በ1894 ነበር። በዚሁ ጨዋታ ቡድኖቹ ሶስት አቻ ተለያይተዋል።

ቡድኖቹ ከመጀመሪያ ጨዋታቸው አንስቶ ለ130 ዓመታት የቆየ ፉክክር በእንግሊዝ እና በአውሮፓ መድረክ አድርገዋል።

በተለይም እ.አ.አ በ199ዎቹ ማብቂና እና በ2000 መጀመሪያ ላይ የባለንጣነት ስሜታቸው እያደገ መጥቷል። 

ማንችስተር ዩናይትድ በሰር አሌክስ ፈርጉሰን እንዲሁም አርሰናል በአርሰን ቬንገር በሚመሩበት ወቅት የነበራቸው ፉክክር የሚዘነጋ አይደለም።

አርሰናል የሊጉን ዋንጫ 13 ጊዜ ሲያነሳ ማንችስተር ዩናይትድ 20 ጊዜ በማንሳት የበላይነቱን ይዟል።

ሚኬል አርቴታ የተጋጣሚያቸው ቡድን አሰልጣኝ ሩበን አሞሪም ማንችስተር ዩናይትድን በአጭር ጊዜ ውስጥ አሻራቸውን አሳርፏል፣ ለተጫዋቾቹ አዲስ ኃይል ይዞ መጥቷል ሲል ከጨዋታው በፊት በሰጠው መግለጫ አሞካሽቶታልደ

ማንችስተር ዩናይትድ ጥሩ ቢሆንም እኛ በራሳችን ጨዋታ ላይ አተኩረን ለማሸነፍ እንጫወታለን ብሏል።

ሩበን አሞሪም ከጨዋታው በፊት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አርሰናል እኔ አሰልጣኝ ከሆንኩ በኋላ የምገጥመው ትልቁ ቡድን ነው፣ ሁሉም ጨዋታ ፈተና ያለበት ነው ለዛም ተጫዋቾቼ እንዲዘጋጁ ጥረት እያደረጉ ነው ብሏል።

በጨዋታው ጠንካራ ተነሳሽነት ማሳየት ይጠበቅብናል፣ ለጨዋታው የራሳችንን የአጨዋወት ስልት ይዘን ወደ ሜዳ ይዘን እንገባለን ሲል ገልጿል። 

የ30 ዓመቱ ሳም ባሮት የሁለቱን ክለቦች ተጣባቂ ጨዋታ በዋና ዳኝነት ይመሩታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም