ቀጥታ፡

ሰባት ጎሎችን ባስተናገደው የሊጉ ተጠባቂ ጨዋታ መቻል ቅዱስ ጊዮርጊስን አሸነፈ 

አዲስ አበባ፤ ህዳር 24/2017(ኢዜአ):- በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ10ኛ ሳምንት ሁለተኛ ጨዋታ መቻል ቅዱስ ጊዮርጊስን 4 ለ 3 አሸንፏል።

ማምሻውን በድሬዳዋ ስታዲየም የተካሄደው ጨዋታ አዝናኝ፣ ተመጣጣኝ ፉክክር የታየበት እና የተመልካቾችን ቀልብ የሳበ ነበር።

በረከት ደስታ፣ ሽመልስ በቀለ እና ጋናዊው ፍሪምፖንግ ሜንሱ በጨዋታ እንዲሁም ምንይሉ ወንድሙ በፍጹም ቅጣት ለመቻል የማሸነፊያ ግቦቹን ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።

አማኑኤል ኤርቦ እና ቢኒያም ፍቅሩ በጨዋታ፣ ፍጹም ጥላሁን በፍጹም ቅጣት ምት ለቅዱስ ጊዮርጊስ ጎሎቹን አስቆጥረዋል።

ውጤቱን ተከትሎ መቻል ነጥቡን ወደ 20 ከፍ በማድረግ የሊጉን መሪነት አጠናክሯል። በውድድር ዓመቱም ስድስተኛ ድሉን አስመዝግቧል።

በአንጻሩ በውድድር ዓመቱ ሶስተኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው ቅዱስ ጊዮርጊስ በ11 ነጥብ ከነበረበት 9ኛ ደረጃ ወደ 11ኛ ዝቅ ብሏል።

ቀን ላይ በተካሄደ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ10ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ጨዋታ ድሬዳዋ ከተማ ሲዳማ ቡናን 3 ለ 1 አሸንፏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም