በክልሉ ሙስናን በዘላቂነት ለመከላከል እየተደረገ ያለውን ጥረት በመደገፍ አጋር አካላት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ሙስናን በዘላቂነት ለመከላከል እየተደረገ ያለውን ጥረት በመደገፍ አጋር አካላት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ተጠየቀ
ባህር ዳር ፤ ህዳር 24/2017 (ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል ሙስናና ብልሹ አሰራርን በዘላቂነት ለመከላከል እየተደረገ ያለውን ጥረት በመደገፍ አጋር አካላት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ተጠየቀ።
የክልሉ ስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ሙስናን ለመከላከል በስነ-ምግባር ግንባታ፣ የተቋም አሰራር ስርዓት ጥናትና የሃብት ምዝገባ ላይ በማተኮር እየሰራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
የፀረ-ሙስና ቀንን አስመልክተው የክልሉ ስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ሀብታሙ ሞገስ ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፤ ሙስና በመታገል የሁሉም ዜጋ ሃላፊነት ሊሆን ይገባል።
ሙስናን በአንድ ተቋም ብቻ ለመከላከል አስቸጋሪ በመሆኑ የአጋር ተቋማት ያልተቆጠበ ድጋፍና እገዛ ወሳኝነት እንዳለው ገልጸዋል።
በተለይም የዴሞክራሲና የሃይማኖት ተቋማት እንዲሁም የመገናኛ ብዙሃንና የፍትህ አካላት ሙስናን በዘላቂነት ለመከላከል በሚደረገው ርብርብ ሁሉ ሚናቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
ወጣቶችና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች ሙሰኞችንና ሌቦችን በመጠቆም የፀረ-ሙስና ትግሉን ለማሳካት ማገዝ እንዳለባቸውም አመልክተዋል።
ኮሚሽኑ በስነ-ምግባር ግንባታ፣ የተቋም አሰራር ስርዓት ጥናትና የሃብት ምዝገባ ስራዎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝም አስታውቀዋል።
በመንግስት ተቋማት የሚታዩ የአገልግሎት አሰጣጥ፣ መልካም አስተዳደር ችግርና ብልሹ አሰራሮችን ለማስተካከል የተለያዩ ሪፎርሞችን እየተተገበሩ እንደሚገኙም ገልጸዋል።
በክልሉ ህዳር 27/2017 ዓ.ም "ወጣቶችን ያማከለ የፀረ-ሙስና ትግል የነገን ስብዕናን ይገነባል "በሚል መሪ ሀሳብ የዓለም የፀረ-ሙስና ቀን ምክንያት በማድረግ ስፖርታዊ ውድድሮች፣ የፅዳት ዘመቻዎች፣ የህዝብ ውይይት መድረኮችና የሃብት ምዝገባ ተግባራት እንደሚከናወኑ አብራርተዋል።