ቀጥታ፡

የኢቢሲ ወላይታ ሶዶ ስቱዲዮ መከፈት ህዝብን በነጠላ ትርክት ለመነጣጠል የሚፈልጉ አካላትን ለመታገል ጠቀሜታው የጎላ ነው-አቶ ጥላሁን ከበደ 

ሶዶ ፤ህዳር 24/2017 (ኢዜአ)፦የኢቢሲ ወላይታ ሶዶ ስቱዲዮ መከፈት  ህዝብን በነጠላ ትርክት ለመነጣጠል የሚፈልጉ አካላትን ለመታገል ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ ገለጹ።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማህበራዊ ዘርፍ አማካሪ ሚንስትር ሙአዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በበኩላቸው፣ በሁሉም አቅጣጫ ኢትዮጵያውያን አንድነታቸውን አጠናክረው በጋራ ሊቆሙ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) በወላይታ ሶዶ ከተማ ያስገነባውን ስቱዲዮ ዛሬ አስመርቋል።


 

በምረቃ ሥነ ስርዓቱ ላይ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ እንደገለጹት፤ በነጠላ ትርክት እርስ በእርስ የተጋመደና የቱባ እሴቶች ባለቤት የሆነውን ህዝብ ለመነጣጠል የሚሞክሩ አካላት አሉ። 

ነጠላ ትርክት ፈጥረው ህዝብን ሊነጣጥሉ የሚፈልጉ አካላትን በአብሮነት መታገል እንደሚገባ ጠቅሰው፤  እነዚህን አካላት ለመታገል ኢቢሲ በወላይታ ሶዶ ከተማ የገነባው ስቱዲዮ የጎላ ጠቀሜታ እንዳለው አመልክተዋል።

  በርካታ የተፈጥሮ፣ የባህልና የታሪክ እሴቶች ባለቤት የሆኑ ህዝቦች ያሉበትን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከፍ ለማድረግ ያለው አስተዋጽኦም የላቀ መሆኑን ነው የተናገሩት።

እውነተኛ መረጃን ለህዝቡ በማድረስ ክልሉን የሰላም ተምሳሌት ለማድረግ ስቱዲዮውን በአግባቡ ልንጠቀምበት ይገባል ብለዋል።


 

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማህበራዊ ዘርፍ አማካሪ ሚኒስትር ሙአዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በበኩላቸው፤ ለጠላት በር ላለመክፈት አንዳችን ለአንዳችን ከመቆም ባለፈ ተባብረን መስራት አለብን ብለዋል።

በሁሉም የአገሪቷ አካባቢዎች ኢትዮጵያውያን ህብረታቸውን በማጠናከር በጋራ ሊቆሙ ይገባል ሲሉም ገልጸዋል።

አንድ ሆነን ከተባበርንና ከተጋገዝን ማንም ሊነካን አይችልም ሲሉም አክለዋል።


 

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) በበኩላቸው እንዳሉት፣ አገራዊ ብልጽግና ማምጣት የሚቻለው የኢኮኖሚ ልዕልናን በማረጋገጥ ተረጂነትን የሚጸየፍ ማህበረሰብ ማፍራት ሲቻል ነው።

የወላይታ ሶዶ ኢቢሲ ስቱዲዮ በክልሉ የተለያዩ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦችን ባህላዊ እሴቶች እና የክልሉን እምቅ ሀብት በማስተዋወቅ የኢትዮጵያን ልዕልና ለማረጋገጥ የሚሰራበት መሆን እንዳለበት ተናግረዋል።

ስቱዲዮው ብልጽግናን የሚናፍቅና ተረጂነትን የሚጠየፍ ትውልድ ለመገንባት መሳሪያ መሆኑን በማከል።


 

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ እውነቴ አለነ በበኩላቸው እንዳሉት፤ ስቱዲዮው በሀገረ መንግስት ግንባታ ሂደት የራስን ድርሻ ለመወጣት፣ የተሳሳቱ ትርክቶችን ለማረምና አሰባሳቢ ትርክቶችን ለመገንባት የሚያስችል ነው።


 

የብልጽግና ፓርቲ የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ኃላፊ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ስቱዲዮው የደቡብ ኢትዮጵያን የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ እሴቶችና ቅርሶችን ኢቢሲን በመጠቀም ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማስተዋወቅ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

ማህበረሰቡና አመራሩ ስቱዲዮውን በመጠቀም የኢትዮጵያን ጸጋ አውጥቶ የሚናገርበትና ህብረ ብሔራዊ አንድነቱ የሚገነባበት ሊሆን እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

በመላ አገሪቷ ኢቢሲ እየገነባ ያለው ስቱዲዮ በሀሳብ ልዕልና የሚያምኑ፣ ከውሸት ይልቅ እውነትን የሚያስቀድሙ አትዮጵያውያንን ለማፍራት ፋይዳው የላቀ ነው ሲሉም ገልጸዋል።


 

የኢቢሲ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጌትነት ታደሰ በበኩላቸው፣ ኢቢሲ በሁሉም አካባቢዎች ተገኝቶ ዘገባዎችን በመስራት በአፍሪካ ደረጃም እንደ ህዝብ ለመደመጥ በሚሰራው ስራ አመራሩ ድጋፍ ሊያደርግ ይገባል ብለዋል።

በስቱዲዮ የምረቃ ሥነ ስርዓት ላይ የፌዴራልና የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ከፍተኛ አመራር አባላትና የሶዶ ከተማ የህብረተሰብ ተወካዮች ተገኝተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም