ቀጥታ፡

የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል ምክንያት በማድረግ በአርባምንጭ ከተማ የንግድ ትርኢትና ባዛር ተከፈተ

አርባምንጭ፤ ህዳር 24/2017(ኢዜአ)፦ ህዳር 29 የሚከበረውን የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል ምክንያት በማድረግ በአርባ ምንጭ ከተማ የተዘጋጀውን የንግድ ትርዒትና ባዛር የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ጥላሁን ከበደ በይፋ መርቀው ከፈቱ።

አቶ ጥላሁን በዚሁ ወቅት በአርባምንጭ ከተማ የተከፈተው ሀገር አቀፍ የንግድ ትርኢትና ባዛር የህዝቡን ኢኮኖሚ ከማነቃቃት በላይ አብሮነትና አንድነትን ለማጠናከር የጎላ ፋይዳ አለው ብለዋል።

ክልሉን የሰላም፣ የመቻቻልና የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ ሰፊ ተግባራት እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፤ "ይህን ሊያሳካ የሚያስችል ሰፊ ፀጋ አለ" ብለዋል።

በንግድ ትርኢትና ባዛሩ ላይ ከመላው ሀገሪቷ የተለያዩ ኢንተርፕራይዞችና የንግድ ድርጅቶች ባቀረቡት ምርት መደነቃቸውን ጠቅሰው፤ "በርትተን ከሠራን ከተስፋ ወደሚጨበጥ ብልጽግና ለመሸጋገር ጊዜው አጭር ነው" ብለዋል።

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የግብርና ምርቶች እሴት በመጨመር እንዲሁም የተኪና ወጪ ምርቶች በስፋት እንዲመረቱ ሰፊ ዕድል ፈጥሯል ነው ያሉት።

የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦችን በዓል በተለያዩ ሁነቶች ማክበር በህዝቦች መካከል መነቃቃትና የጋራ መግባባት ከመፍጠር አንጻር የጎላ ሚና እንደሚጫወትም አስረድተዋል።

በተጨማሪም የወንድማማችነትና እህትማማችነት የጋራ ትርክቶች ሥር እንዲሰዱ የሚያግዝ እንደሆነም ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል።


 

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ ገሌቦ ጎልቶሞ በበኩላቸው በዓሉ የንግድ ግብይት፣ ኢንቨስትመንትና የወጪ ንግድ ሀብቶቻችንን ለማስተዋወቅ ልዩ ዕድል የሚፈጥር ነው ብለዋል።

ኢንተርፕራይዞች የገበያ ትስስር ለመፍጠር ብሎም ገበያን ለማረጋጋት ትልቅ ፋይዳ እንዳላቸው በማከል።

ቢሮው የዘመነና ፍትሃዊ የንግድ ስርዓት ለማጠናከር እየሠራ መሆኑን ጠቅሰው፤ ኢንተርፕራይዞችና ነጋዴዎች የንግድ ህጎችን አክብረው በመስራት የበኩላቸውን እንዲወጡ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል የኢኮኖሚያዊና ባህላዊ ፀጋዎቻችንን ለማስተዋወቅ ብሎም ልምድ ለመለዋወጥ የሚግዝ ነው ያሉት ደግሞ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ቦጋለ ቢታኔ ናቸው።

ሥራ ፈጣሪነትና የገበያ ዕድሎችን የሚፈጥር በመሆኑም ሥራ ፈጣሪዎችና ሸማቾች ይህን ዕድል መጠቀም እንዳለባቸው አሳስበዋል።

በአርባምንጭ ከተማ ዛሬ የተከፈተው የንግድ ትርኢትና ባዛር ለአንድ ሳምንት የሚቆይ ሲሆን ከ150 በላይ ኢንተርፕራይዞችና የንግድ ድርጅቶች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም