ቀጥታ፡

የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎትና የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን ሥምምነት ተፈራረሙ

አዲስ አበባ፤ህዳር 24/2017(ኢዜአ)፦የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎትና የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ሥምምነት ተፈራረሙ።

ስምምነቱን የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሙሉቀን አማረና የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ሃላፊ ቢኒያም ምክሩ ፈርመውታል።

ስምምነቱ ሁለቱ ተቋማት በቅንጅት የሚያከናውኗቸውን ተግባራት ውጤታማነትን ለማጎልበት የሚያስችል እንደሆነ ተገልጿል።

ስምምነቱ በአዲስ አበባ ከተማ የታክስ ስወራን ለመከላከልና ነጋዴዎች ፍትሃዊ ታክስ እንዲከፍሉ ለማድረግ አላማ ያደረገ እንደሆነ ተመላክቷል።

የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሙሉቀን አማረ በዚሁ ጊዜ እንደገለፁት፥ አገልግሎቱ በፋይናንስ ዘርፉ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን በመከላከል አገሪቱ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እንድታገኝ እየሰራ ነው።

በህገ-ወጥ መንገድ የተገኘን ገንዘብ ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መደገፍን የመከላከል ስራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ስምምነቱ በአዲስ አበባ ከተማ የታክስ ስወራን ለመከላከል፣ ታክስ ሳይከፍሉ ገንዘብ የደበቁ ወይም ያሸሹ አካላት እንዲከፍሉና ተጠያቂ እንዲሆኑ በጋራ ለመስራት የሚያስችል እንደሆነ ገልፀዋል።

ስምምነቱ ሁለቱ ተቋማት ጥናትን መሰረት ያደረገ የቅንጅትና የትብብር ስራን በማከናወን መዲናዋ ማግኘት የሚገባትን ገቢ እንድታገኝ ለማድረግ እንደሚያስችልም ጠቁመዋል።

የታክስ ስወራና ሌሎች የፋይናስ ወንጀሎችን በመከላከል አገሪቱ በበጀት አመቱ ያስቀመጠችውን የገቢ ዕቅድ እንድታሳካ የትብብር ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ገቢዎች ቢሮ ሃላፊ ቢኒያም ምክሩ በበኩላቸው መዲናዋ የጀመረችውን ልማት አጠናክሮ ለማስቀጠል የገቢ አሰባሰቡን ለማሳደግ የሚያስችሉ ስራዎች እየተሰሩ ነው።

በዚህም በበጀት አመቱ የተያዘውን 230 ቢሊዮን የገቢ እቅድ ለማሳካት ውጤታማ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አስረድተዋል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም