አካል ጉዳተኞች በሁሉም ዘርፎች እኩል ተደራሽና ተጠቃሚ እንዲሆኑ መላው ማህበረሰብ ተግባራዊ ምላሽ እንዲሰጥ ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
አካል ጉዳተኞች በሁሉም ዘርፎች እኩል ተደራሽና ተጠቃሚ እንዲሆኑ መላው ማህበረሰብ ተግባራዊ ምላሽ እንዲሰጥ ተጠየቀ
ሀዋሳ፣ህዳር 24/2017 (ኢዜአ)፦አካል ጉዳተኞች በአገልግሎቶችና እድሎች እኩል ተደራሽና ተጠቃሚ እንዲሆኑ መንግስትና መላው ህብረተሰብ ተግባራዊ ምላሽ መስጠት እንደሚጠበቅበት ተገለፀ።
ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን የማጠቃለያ ፕሮግራም በአገር አቀፍ ደረጃ "የአካል ጉዳተኞችን የመሪነት ሚና በማጉላት አካታችና ዘላቂ ልማትን እናረጋግጥ" በሚል መሪ ሐሳብ ዛሬ በሀዋሳ ከተማ በተለያዩ ሁነቶች ተከብሮ ውሏል።
የኢፌዴሪ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ(ዶ/ር) በዓሉ በየዓመቱ ሲከበር ለማህበረሰቡ ግንዛቤ እና አካታች ማህበረሰብ ከመፍጠር አኳያ መሠረት አድርጎ ነው ብለዋል።
የአካል ጉዳተኞች ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት የማረጋገጥ ጉዳይ ያለሰለሰ ጥረት የሚጠይቅ በመሆኑ ሁሉም ይህን በመገንዘብ የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባ አስታውቀዋል።
እንደሀገር የአካል ጉዳተኞች ተሳታፎና ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ አንጻር ውጤታማ ለውጦች መኖራቸውን አውስተው፤ ይህን ማጠናከር ይገባል ብለዋል።
በዚህ ረገድ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም መላው ህብረሰብ ንቁ ተሳትፎና ተግባራዊ ምላሽ መስጠት እንደሚጠበቅባቸው ኤርጎጌ (ዶ/ር) አሳስበዋል።
በዚህ ረገድ መሪ ቃሉም እንደ ሀገር የአካል ጉዳተኞች የአመራር ሰጪነት ሚና በማጎልበት ሂደት ውጤታማ ስራ እንድንሰራ የሚያነሳሳንና ጉልበት የሚሰጠን ነው ሲሉ ሚኒስትሯ አስታውቀዋል።
በተለይም በአሉን ስናከብር አካል ጉዳተኞች የተለያዩ ተግዳራቶችን በጽናት በማለፍ ያስመዘገቡትን ስኬትም የምንዘክርበት ነው ብለዋል።
የሲዳማ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ በበኩላቸው በአካል ጉዳተኞች ላይ የማህበረሰቡን ግንዛቤ ለማሻሻል ብዙ ስራዎች ቢከናወኑም አሁንም ቀሪ ስራዎች ይጠብቅብናል ብለዋል።
አካል ጉዳተኝነት የየዕለት ህይወታችንና የማህበረሰቡ አካል መሆኑን መቀበል ይገባል ነው ያሉት።
በመሆኑም ከተንሸዋረረ እይታና ተግባር ፈጥኖ በመላቀቅ ከአካል ጉዳተኞች ጋር በመተባበርና ከጎናቸው በመሆን አጋርነታችንን በተግባር ማሳየት ከሁሉም ይጠበቃል ብለዋል።
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ ማህበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ታደለ ቡርቃ(ዶ/ር) አካል ጉዳተኞችን ጉዳይ አካቶ መስራት ለሁሉም የመንግሥት ተቋማት በአዋጅ የተሰጠ ኃላፊነት መሆኑን አስታውቀዋል።
በመሆኑም ሁሉም ተቋማት አካል ጉዳተኝነት ጉዳይ የእቅዳቸው አካል በማድረግ ለተፈጻሚነቱ በተቀናጀና በተናበበ መንገድ ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበው ለዚህም ምክር ቤቱ የቅርብ ክትትልና ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
በበዓሉ ላይ የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን፣ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ተወካይ፣ የሁሉም ክልሎች የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ሃላፊዎች፣ የአካል ጉዳተኞች ማህበራት ተወካዮች እንዲሁም ሌሎችም ጥሪ የተደረገላቸው ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።