ቀጥታ፡

የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን በአደባባይ መከበሩ ባህል እና እሴቶቻችንን ለማስተዋወቅ ያግዛል

አሶሳ፤ ህዳር 24/2017(ኢዜአ)፦ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን በአደባባይ መከበሩ ባህል እና እሴቶቻችንን ለማስተዋወቅ ያግዛል ሲሉ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በበዓሉ ላይ የታደሙ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተናገሩ።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ደረጃ የ19ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን ማጠቃለያ በዓል በክልሉ ኡራ ወረዳ በአደባባይ ተከብሯል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የክልሉ ታዳሚዎች እንዳሉት የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን በአደባባይ መከበሩ ባህል እና እሴቶቻችንን ይበልጥ ለማስተዋወቅ እድል ይፈጥራል ብለዋል።

ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ ኑረዲን ነጉራ እንዳሉት ቀኑ በአደባባይ ሲከበር ብሄሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች የኢትዮጵያን መልክ የሚያሳዩበት አጋጣሚ ይፈጠራል፤ እንዲሁም የባህል ትውውቅ ይደረጋል ብለዋል።

የማኦ ብሄረሰብን ወክለው በበዓሉ ላይ የተገኙት አቶ ኑረዲን በብሄሮች፣ ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ቀን ብሔረሰቡ የራሱን ማንነት እና እሴት በሀገር አቀፍ ደረጃ እያስተዋወቀ ይገኛል ብለዋል።

ሌላዋ የበዓሉ ተሳታፊ ወይዘሮ የምስራች ሙስጠፋ በበኩላቸው ክልሉ የተለያዩ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦች እና ህዝቦች በጋራ የሚኖሩበት መሆኑን ጠቅሰው፤ ቀኑ አብሮነታቸውን ለማደስ መልካም አጋጣሚ እንደሆነ ገልፀዋል።


 

በብሄሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን የታየውን አብሮነት "ለሰላም እና ለልማት ልንጠቀምበት ይገባል" ያሉት ደግሞ አቶ ኩሹሽ ፍቃዱ ናቸው።


 

ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች በራሳቸው ባህላዊ አለባበስና ጌጣጌጥ በአንድ ላይ ሲሆኑ የተለየ ውበት እንደሚፈጥርም ገልፀዋል።

በበዓሉ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት አፈጉባኤ ወይዘሮ አስካል አልቦሮ፤ ቀኑ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ለሀገራቸው ዋስትና መሆናቸውን የሚያረጋግጡበት ነው ብለዋል።


 

በተለይም ቀኑ በክልሉ ኡራ ወረዳ በአዳባባይ ሲከበር የወረዳውን እምቅ የተፈጥሮ ሀብቶች በማስተዋወቅ በኩልም የራሱ አስተዋፅኦ እንዳለው ጠቁመዋል።

በብልፅግና ፓርቲ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኢሳቅ አብዱልቃድር በበኩላቸው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን መከበር ለጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታ እና ህብረ ብሔራዊ ፌዴራሊዝም እንዲጎለብት ማድረጉን አብራርተዋል።


 

በዕለቱ የተለያዩ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ባህላዊ ጭፈራዎቻቸውን እና እሴቶቻቸውን ለታዳሚው አቅርበዋል።

የ19ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን በአርባ ምንጭ ከተማ ከነገ ህዳር 25 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚከበር ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም